ብርሀኑ ግዛው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ተሾሙ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ብርሀኑ ግዛውን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በማድረግ ሾሟል፡፡

በቀጣዩ ወር ኅዳር መጀመሪያ ላይ በታንዛኒያ አስተናጋጅነት የሴካፋ የሴቶች ዋንጫ ውድድር የሚደረግ ሲሆን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችም ይከተላሉ። በቅርቡ ከአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ጋር የተለያየው ፌዴሬሽኑም ለውድድሮቹ ዝግጅት እንዲረዳው ብርሀኑ ግዛውን በዋና አሰልጣኝነት መሾሙን አሰልጣኙ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በየካ እና ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ክለቦች እንዲሁም ከ2004 ጀምሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም በሊሱዎቹ የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እና አብርሀም ተክለሀይማኖት ረዳትነት እንዲሁም በ2008 በዋና አሰልጣኝነት ሰርተዋል፡፡

አሰልጣኙ ነገ ረዳቶቻቸውን እና የተመረጡ ተጫዋቾችን ይፋ የሚያደርጉ ሲሆን ዝግጅታቸውን ደግሞ በዚህ ሳምንት ሀዋሳ ወይም አዲስ አበባ ላይ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ሰምተናል፡፡

ኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በታንዛኒያ በሚካሄደው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ላይ በምድብ ለ ከዩጋንዳ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ ጋር መደልደሉ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ