አስቻለው ታመነ እና ጌታነህ ከበደ ለትውልድ ከተማቸው ክለብ ድጋፍ አደረጉ

ከዲላ ከተማ የተገኙት እና በቅዱስ ጊዮርጊስ እየተጫወቱ የሚገኙት አስቻለው ታመነ እና ጌታነህ ከበደ ለጌዲኦ ዲላ እግር ኳስ ክለብ የቁሳቁስ ድጋፍን አድርገዋል።

ዲላ በሚገኘው ዲ ላይት ሆቴል እሁድ አመሻሹን በነበረው በዚህ ሥነስርዓት ላይ የጌዲኦ ዞን አስተዳዳሪ እና የክለቡ የበላይ ጠባቂ አቶ ገዙ አሰፋ፣ የክለቡ ፕሬዝዳንት ነፃነት ታደለ እና ስራ አስኪያጁ ተዘራ ጌታሁን፣ አስቻለው ታመነ እና የጌታነህ ከበደ ተወካይ ወንድሙ ተስፋዬ ከበደ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሁለቱም ፆታ የጌዲኦ ዲላ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ተገኝተዋል፡፡

የክለቡ ስራአስኪያጅ አቶ ተዘራ ጌታሁን ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስቻለው ታመነ እና ጌታነህ ከበደ በተወለዱበት ከተማ በመገኘት ክለቡን ለማበረታታት በርካታ ገንዘብ ፈሰስ በማድረግ ክለቡን በተደጋጋሚ እየደገፉ በመገኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው በመተባበር እና በመተጋገዝ ክለቡን ከሌላው ጊዜ በበለጠ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደተነሱ በንግግራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በመቀጠል የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ነፃነት በበኩላቸው በተደረገው ነገር ሁሉ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ከተጫዋቾቹ መልካም ተግባር ሁሉም ሊማር ይገባል ሲሉም ገልፀዋል፡፡ የእለቱ የክብር እንግዳ እና የክለቡ የበላይ ጠባቂ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው ” ዞናችን ፍሬዋን እያየች በመሆኑ ሁላችንም ከሌላው ጊዜ በበለጠ ተነሳሽነታችን ጨምሮ የነኚህን ወጣቶች መልካም ተግባር ለመፈፀም ዝግጁ መሆን አለብን። ዘንድሮ የጌዲኦ ዲላ የወንዶች ቡድን ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ያሰበ በመሆኑ ክለቡን ለመደገፍ በጋራ ርብርብ ማድረግ አለብን።” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አቶ ገዙ አክለው በቅርቡ ለተጫዋቾቹ ለየት ያለ ሽልማትን በዞን ደረጃ ተፈፃሚ ለማድረግ እንዳሰቡም ጠቁመዋል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ አስቻለው ታመነ ባደረገው ንግግር “የከተማው ነዋሪ እኛ ያደረግን አይቶ ከሌላው ዓመታት በተሻለ ባለሀብቱም ሆነ ማንኛውም የክለቡ ወዳድ ድጋፋችሁን ያለ ስስት መለገስ አለባችሁ። ተጫዋቾችም ራሳችሁን ጠብቃችሁ ቡድኑ ከናንተ የሚፈልገውን ስለሚጠብቅ ዲሲፕሊንድ በመሆን ክለቡን ወደ ፕሪምየር እንዲገባ የተቻላችሁን ሁሉ እንድትፈፅሙ አደራ እላለሁ።” በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡ አስቻለው በንግግሩ ማብቂያም “ከተማው ለወጣቶች ትኩረት ሰጥቶ ከአሁን በኋላም ሊሰራ ይገባል አቅም ያላቸው ተጫዋቾች እዚህ ስላሉ ኃላፊነት ያለባችሁ ትኩረት እንድትሰጡ በድጋሚ አሳስባለሁ።” ብሏል፡፡ የጌታነህ ከበደ ተወካይ ተስፋዬ ከበደ በበኩሉ “ጌታነህ ከዚህ በፊት ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አሁንም አጠናክሮ እንደሚያደርግ እና የማይቋረጥ የክለቡን ፍቅርም በተግባር ለማገዝ መነሳቱን አስተላልፍልኝ ብሎኛል።” በማለት ተናግሯል፡፡

ከንግግሮቹ በመቀጠል አስቻለው ታመነ እና ጌታነህ ከበደ ከ240 ሺህ ብር በላይ በማውጣት የገዙትን በሁለቱም ፆታ ለሚገኙ የክለቡ ተጫዋቾች 20 ኳሶች 60 ቢብሶች ከ50 በላይ የመጫወቻ ጫማዎችን ያበረከቱ ሲሆን አስቻለው ታመነ ደግሞ ከጌታነህ ከበደ ጋር በጋራ ካደረገው ድጋፍ ውጪም በስሩ ለሚደግፋቸው እና በተለያዩ የተስፋ ቡድኖች ውስጥ ለሚጫወቱ አምስት ታዳጊዎች የመጫወቻ ጫማ እንዲሁም በዲላ ከተማ ውስጥ ታዳጊዎች በማሰልጠን እየሰራ ላለው ወጣት አሰልጣኝ ይብራ መሀሪ የአምስት ኳሶች ስጦታ ያበረከተ ሲሆን ለጌዲኦ ዲላ የወንዶች ቡድን አሰልጣኝ ደረጀ በላይ እና ለሴት ቡድን አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካም የማሰልጠኛ ቁሳቁስ አበርክቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ