አብርሃም መብራቱ በወቅታዊ የብሔራዊ ቡድን ጉዳዮች ዙርያ ገለፃ ሰጥተዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና የቡድኑ አምበል አስቻለው ታመነ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ እና በቻን ማጣርያ ስለነበራቸው ጉዞ በዛሬው ዕለት በፌዴሬሽኑ አዲሱ ህንጻ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫው በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦችን እንደሚከለው አቅርበነዋል።

ከሌሶቶ ብሔራዊ ቡድን ጋር ስለነበረው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ

“በሌሶቶው ጨዋታ ያስመዘገብነው ውጤት ለሁሉም እንደጥሩ ውጤት የሚጠቀስ ነው፤ በድምር ውጤት ወደ ምድብ ድልድሉ የገባንበትን ውጤት ማስመዘገብ ችለናል፡፡ ይህም ፈርጀ ብዙ ጥቅሞችን የሚያስገኝልን ይሆናል፤ በአዲስ መልኩ በወጣቶች እየተገነባ ለሚገኘው ብሔራዊ ቡድናችን ከሚያስገኘው ጥቅሞች መካከል በምናገኛቸው ተጨማሪ ጨዋታዎች በዓለምአቀፍ የውድድር መድረክ ተጫዋቾች ለመሞከርና ልምድ እንዲያገኙ የራሱን ሚና ይወጣል። በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለጀመርነው በውጭ ሀገራት የሚገኙ ተጫዋቾች ሀብትን ለመጠቀም በዚህ ውድድር ላይ ይበልጥ ተሳታፊ በማድረግ ተጠቃሚ ልንሆንበት የምንችለውን ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ በዓመቱ ውስጥ የምናደርጋቸውን የዓለምአቀፍ ጨዋታዎች ቁጥር መጨመሩ ለስፖርት ቤተሰቡም ሆነ ለተጫዋቾቹ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው፡፡

“በሌሶቶው የደርሶ መልስ ጨዋታ ውጤት እንድናስመዘገብ ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት ተጫዋቾቹን በዚህ አጋጣሚ ለማመስገን እወዳለሁ ፤ በማሸነፍ ሥነልቦና ከየቱም ጊዜ ልቀው የተገኙበት ሂደት የሚያስመሰግን ነው። ከሜዳ ውጭ የነበሩትን አሉታዊ ሁነቶች ወደ በጎ ሁኔታ በመቀየር ያስመዘገቡት ነገር ተስፋ ሰጪ አጋጣሚ ነበር፡፡”

በቻን ስለነበራቸው አጠቃላይ ጉዞ

“የውድድሩ ፕሮግራም በድንገት ስለወጣ ዝግጅታችን አጭር ነበር፤ በመጀመሪያው የጅቡቲ ጨዋታ ከሜዳ ውጭ በነበረን የተሻለ ስነልቦና አሸንፈን ልንመጣ ችለናል። በመልሶ ጨዋታ ግን በውጤቱ ብናሸንፍም በቡድኑ እንቅስቃሴ ደስተኛ አልነበርንም፡፡ ከዛ በመነሳት የነበሩ ችግሮችን ለማረም በተለይም በአካል ብቃት የነበሩብን ክፍተቶችን አርመን ለሩዋንዳው ጨዋታ የተሻለ ቡድን ይዘን መቅረብ ችለናል፡፡ በመቐለው ጨዋታ ከመጀመሪያው የማጣርያ ጨዋታ በተሻለ ብዙ የጨዋታ ብልጫ ቢኖርም እድለኛ ስላልነበርን በሜዳችን ማግኘት የነበረብንን ነገር አለማሳካታችን ዋጋ አስከፍሎናል። በመልሱ ጨዋታ በሜዳችን ካደረግነው በተሻለ ሙሉ ለሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥረን መጫወት ብንችልም በሁለት ምክንያቶች ከውድድሩ ልንወጣ ችለናል፡፡ አንደኛው የተጫዋቾች ልምድ ማነስ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በመጠነኛ የተከላካዮች ትኩረት ማነስ የተነሳ ያሰብነውን ማሳካት ሳንችል ቀርተናል

“የሩዋንዳው ጨዋታ ውጤት አጠቃላይ የቡድኑን ሁኔታ አይገልፅም፤ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ነበረን፡፡ ቡድኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠንካራ ቡድን ግንባታ ሂደት ላይ እንዳለ ማሳያ የሚሆን ጨዋታ ነበር፡፡ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ከሜዳ ውጭ በሥነልቦና በማሸነፍ ተነሳሽነት ተሽለን የቀረብንበት ሂደትን ማየት ይቻላል። ቡድኑ ከ90% በላይ በወጣቶች የተገነባ ቡድን ነው በሩዋንዳው ጨዋታም 3(4) የመጀመሪያ ጨዋታ ያደረጉ ወጣት ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ወደፊት እነዚህ ተጫዋቾችን ከነባር ተጫዋቾች ጋር ማቀናጀት ከተቻለ የተሻለ ነገር መስራት እንችላለን፡፡

* በቀጣይ አሰልጣኙ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾች እና የአስቻለው ታመነን አስተያየት ይዘን እንቀርባለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ