“በገባነው ቃል መሠረት ወደ ቻን ማለፍ ባለመቻላችን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ” አስቻለው ታመነ

በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሴሽነረ ፅህፈት ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና የቡድኑ አምበል አስቻለው ታመነ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ እና ቻን ማጣርያ ስለነበራቸው ጉዞ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫው ላይ የቡድኑ አምበል የሆነው አስቻለው ታመነ ተከታዮቹን ሀሳቦች አጋርቷል።

“የሌሶቶው ጨዋታ የቡድኑ መንፈስ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ያሳየ ጨዋታ ነበር፤ ጨዋታውን ለማሸነፍ የነበረው የቡድኑ ፍላጎትና የተነሳሽነት ስሜት በአጠቃላይ የቡድኑ አንድነት በጣም ጠንካራ የሚባል ነበር። በዚህም ወደ ዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያው መቀላቀል ችለናል፡፡

“በቀጣይ ያደረግነው በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ከሩዋንዳ ጋር ያደረግነው ጨዋታ ነበር ፤ መቐለ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ በሜዳችን የጣልነው ውጤት እጅግ የሚያስቆጭ ነበር፡፡ ከመቐለ ጨዋታ በኋላ የተመዘገበው ውጤት በአጠቃላይ የቡድኑን ተጫዋቾች ስሜት የጎዳ ነበር፤ በአሰልጣኙም እንደተገለፀው
የጨዋታው ውጤት ቡድን የሚገልፅ አይደለም፡፡ ነገርግን በሜዳችን የጣልነው ውጤት በእጅጉ ጎድቷናል፡፡

“ቡድኑ በአመዛኙ በወጣቶች የተገነባ ነው ፤ ቡድናችንም በዋነኛነት ጎል የማስቆጠር ችግር አለበት። ይህም በእኔ እምነት በሂደት ተጫዋቾቹ ልምድ እያገኙ ሲመጡ ይቀረፋል፡፡ አሁን ላይ ከጨዋታ ጨዋታ በተወሰኑ መልኩ መሻሻሎች አሉ። ለዚህም የባህር ዳሩ የዩጋንዳ የወዳጅነት ጨዋታ በማሳያነት መቅረብ ይችላል፡፡ በዩጋንዳው ጨዋታ ምንም እንኳን ብንሸነፍም በተጫዋቾች ውስጥ የነበረው ደስ የሚል መንፈስ ነበር፡፡”

“በገባነው ቃል መሠረት ወደ ቻን ማለፍ ባለመቻላችን በቡድኑ ስም ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ፤ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታን ለማረጋጋት ቡድናችንን ውጤታማ ለማድረግ በቡድኑ ተጫዋቾች ውስጥ የተሻለ መነሳሳት ነበር ነገርግን ሊሳካ አልቻለም፡፡”

* በቀጣይ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾችን ይዘን እንቀርባለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ