ወላይታ ድቻ ሁለት ተጫዋቾች አስፈረመ

ወላይታ ድቻ የቀድሞው ተከላካዩ አናጋው ባደግን ወደ ክለቡ ሲመልስ አጥቂው ዳንኤል ዳዊትን የግሉ አድርጓል፡፡

በግራ እና በቀኝ ተከላካይነት መጫወት የሚችለው አናጋው ባደግ ለጦና ንቦቹ ለመጫወት ፊርማውን ያኖረ ተጫዋች ሆኗል፡፡ በወላይታ ድቻ መልካም ጊዜያትን ማሳለፉን ተከትሎ በበርካታ ክለቦች በወቅቱ ቢፈለግም ድሬዳዋ ከተማን መቀላቀል የቻለ ሲሆን የ2011 የውድድር ዓመትን ደግሞ በደቡብ ፓሊስን ቆይታን ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ተጫዋቹ ለመከላከያ ከወር በፊት ለመጫወት ፈርሞ የነበረ ቢሆንም ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ እንደሚወዳደር በመገለፁ ወደ ቀድሞ ክለቡ ድቻ አምርቷል፡፡

ሌላኛው ለክለቡ ፊርማውን ያኖረው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ዳንኤል ዳዊት ነው፡፡ አምና በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ነቀምት ከተማ መልካም የውድድር ዓመትን ያሳለፈ ሲሆን ወደ አርባምንጭ ከተማ ለማምራት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ክለቡ በከፍተኛ ሊግ እንዲቀጥል በመወሰኑ ወደ ወላይታ ድቻ በአንድ ዓመት ውል አምርቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ