ከፍተኛ ሊግ | ለገጣፎ ለገዳዲ የአሰልጣኙን ውል ሲያራዝም አራት ተጫዋቾች አስፈረመ

በ2011 የውድድር ዓመት በዳዊት ሀብታሙ እየተመራ በከፍተኛ ሊግ ውድድር እስከ መጨረሻው ድረስ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ፉክክር ማድረግ የቻለው ለገጣፎ ለገዳዲ አራት ተጫዎቾችን ማስፈረም ሲችል የአሰልጣኙንም ቆይታ አራዝሟል።

ቡድኑን ከተቀላቀሉት ተጫዋቾች መካከል ከዚህ ቀደም ለክለቡ የተጫወቱት ልደቱ ለማ እና ፋሲል አስማማው ይጠቀሳሉ። ቡድኑን ለቆ ወደ ስሑል ሽረ ካመራ በኋላ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ ትልቅ አስታዎፅኦ የነበረው ልደቱ ከዛም ወደ ባህር ዳር ከተማ አቅንቶ ግማሽ የውድድር ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ቀድሞ ክለቡ የሚመልሰውን ዝውውር ማድረግ ችሏል።

እንደ ልደቱ ሁሉ ወደ ቀድሞ ቡድኑ የተመለሰው ፋሲል አስማማው በ2010 የልደቱ ቦታን በመሸፈን የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አግቢ የነበረ ሲሆን በ2011 ውድድር ዓመት በፋሲል ከነማ ቆይታ አድርጎ ወደ ለገጣፎ ተመልሷል።

ሌሎች ክለቡን የተቀላቀሉት በአማካይ ስፍራ ላይ የሚጫወተው ተመስገን አዳሙ ከአክሱም ከተማ እንዲሁም የተከለካይ ስፍራ ተጫዋቹ አብዲሳ ጀማል ከአርሲ ነገሌ ናቸው።

በተያያዘ ቡድኑ የወጣቱ አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ እና የምክትሉ ጥላሁን ተሾመን ውል ሲያድስ የቀድሞው የአየር ሀይል እና የቢሾፍቱ ከተማ ግብ ጠባቂ የነበረውን ፍቃዱ ገብሩን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ