“ቡድኑ በወጣቶች እየተገነባ መሆኑና ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ማሳየቱ በግሌ ደስተኛ ያደርገኛል” አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ እና ቻን ማጣርያ ስለነበረው ጉዞ ከሰጡት መግለጫ በማስከትል በስፍራው ከታደሙ የመገናኛ ብዙሃን አካላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ከተነሱት ጥያቄዎች መካከልም አንኳር አንኳሮቹን በሚከተለው አቅርበናቸዋል፡፡


በሌሶቶ ጨዋታ ወቅት ስለተፈጠረው የጉዞ መስተጓጓልና ተያያዥ ጉዳች

“ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ቡድኑን አደረጃጀት ዘመናዊ ለማድረግ ቃል መግባታችን የሚታወስ ነው፤ የሁሉም ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች የራሳቸው የሆነ የጉዞና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚከታተል ኦፊሰር አላቸው። እንደአጋጣሚ ሆኖ እኛ ይሄን ለማድረግ የታደልን አይደለንም። በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ብሔራዊ ቡድኑ ከፌደሬሽኑ ጋር ጥገኛ ሆኖ ነው እየሰራ የሚገኘው፡፡ በሌሶቶው ጉዞ ላይ የተፈጠረው ሁነት ካጋጠመ በኋላ በቀጥታ ወደዚህ ስንመለስ ያደረግነው ነገር ከፌዴሬሽኑ የበላይ አመራሮች ጋር ተገናኝተን ይህን መሠል ሞራል የሚነካ ግዴለሽነት የተሞላበት አሰራር የብሔራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን የሀገርንም ገፅታ የሚያበላሽ ስለመሆኑ ተነጋግረን ተማነናል። ስለሆነም ይህን መሰል ድርጊት ዳግም እንዳይከሰት፤ ከዚህ ድርጊት ጀርባ የነበሩ ሰዎች ላይ እርምጃም ተወስዷል፡፡ አሁንም ቢሆን ጉዞንና ተያያዥ ጉዳዮችን በቋሚነት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ያስፈልጉታል። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይህን ተግባራዊ ሲያደርግ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ ስለዚህም የተመደበው አስተባባሪ ባለሙያ ልምድ አግኝቶ እንዲሰራ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል። በተጨማሪም ባለሙያው ከዋናው ብሔራዊ ቡድን በተጨማሪም የሌሎችም ቡድኖችን ስራ ደርቦ መስራቱ ጫና ፈጥሯል፡፡”

የእረፍት ወቅት ላይ ብሔራዊ ቡድን ማዘጋጀት ያለው ፈተና

“ለማንኛውም ሙያተኛ ተጫዋቾችን በእረፍት ወቅት ማዘጋጀት በሁለት ምክንያቶች ፈተናዎች አሉት። አንደኛው ተጫዋቾች ዓመቱን ሙሉ ውድድር ላይ ስለሚቆዩ ወደ እረፍት ወቅት ሲመጡ በአብዛኛው አቅማቸውን ጨርሰው ነው የሚመጡት። ሌላው የተጫዋቾች የአካል ብቃት መዘበራረቅ በወጥነት ስራችን እንዳንሰራ ያደርጋል፡፡ በተቻለን መጠን የምንሰጠውን ልምምድ ተመጣጣኝ በማድረግና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጠቀም በጀመርነው የፐርፎርማንስ ትራከር የሚገኙ መረጃዎች በመታገዝ ከአካል ብቃት ባለሙያው ጋር በመሆን የተለዩ ልምምዶችን በመስራት የአካል ብቃት ደረጃቸውን ለማሻሻል ሞክረናል፡፡ ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ቡድናችን ላይ ይታይ የነበረው ከ70 ደቂቃዎች በኃላ የመዳከም ነገርን ለማስወገድ ጥረት በማድረግ የተሻለ 90 ደቂቃ ተንቀሳቅሶ መጫወት የሚችል ብሔራዊ ቡድን ለመስራት ጥረናል፡፡”

የፕሪምየር ሊጉ አለመረጋጋት በብሔራዊ ቡድኑ ላይ ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ

“ጠንካራና የተረጋጋ ሊግ በሌበት ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት ከባድ ነው። ለዚህም ይረዳን ዘንድ ነው ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ የስነልቦና ባለሙያዎች ለተጫዋቾቹ ክፍተቶችን ለመድፈን ስልጠና እንዲያገኙ ያደርገነው። በዚህም የተነሳ ነው ከሀገር ውጭ ባደረግናቸው ጨዋታዎች የተሻለ የስነልቦና ዝግጅት ያደረግነው፡፡”

ስለ ብሔራዊ ቡድኑ የጨዋታ ትንተና

“እያንዳንዱን ያደረግናቸውን ጨዋታዎች ትንተና አልሰራንም፤ ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነት ወስጄ ስራውን መስራት ከጀመርኩበት የቻን የመጀመሪያ ማጣርያ ጀምሮ ያደረግነው የጅብቲውን የደርሶ መልስ ጨዋታ ለመገምገም ሞክረናል። የሩዋንዳውንም ጨዋታ በቅርቡ ከብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመሆን በጋራ እንገመግማለን። በተጨማሪም ከዘንድሮ ጀምሮ የአሰልጣኞች ቡድን አባላትና ሌሎች እምነት ከምንጥልባቸው ባለሙያዎች ጋር በመሆን የጨዋታ ምስል ትንተና መስራት ጀምረናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፐርፎርማንስ ትራከር በመጠቀም የእያንዳንዱ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የአካል ብቃት መረጃ ለክለቦች ጋር መረጃ በመለዋወጥ ለመስራት እንቅስቃሴ ጀምረናል። በሌሎች የግምገማ ውጤቶች ጭምር የገመገምነውን መረጃ ለክለቦች እንልካለን። በብሔራዊ ቡድንና በፕሪምየር ሊጉ ክለቦች መካከል ያለው የስልጠና ሂደት መናበብ ካልቻለ ብሔራዊ ቡድኑም ሆነ ሊጉ መረጋጋት አይችሉም፡፡”

ከሜዳ ውጭ የተሻለ ውጤት ስለማስመዝገብ

“ከሌሶቶ ጋር በምንጫወትበት ወቅት በሜዳው የተገኘውን ተመልካች ለማስደት ከመነጨ ጉጉት የተነሳ ከተፈለገው አጨዋወት ውጪ የመውጣት ሁኔታ ነበር። ለማሳያነትም በባህር ዳሩ ጨዋታ በ41 አጋጣሚዎች ረጃጅም ኳሶች ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክልል ብንልክም 39 ኳሶች ስኬታማ አልነበሩም፤ በሜዳችን ስንጫወት ተጫዋቾች በደጋፊዎቻቸው ስሜት ውስጥ ገብተው ከጨዋታ እቅድ የመውጣት ነገር ይስተዋላል። በተቃራኒው ከሀገር ውጭ በምንወጣበት ወቅት ከተመልካች ከጫና ውጭ ሆነን በጨዋታ እቅዳችን መሠረት ለመጫወት መሞከራችን የተሻለ ብልጫ መውሰድ አስችሎናል፡፡”

እስከአሁን በአሰልጣኝነት ብሔራዊ ቡድኑን ይዘው በመጣው ውጤት ስለሚሰማቸው ስሜት

“ከአሀዛዊ መለኪያዎች አንጻር ከተመለከትነው እኔ ደስተኛ አይደለሁም፤ ነገርግን ከዚህ ባሻገር ውጤቶቹ በተናጥል የቡድን መሻሻል አይጠቁሙም፤ እኔ በግሌ ደስተኛ የምሆንባቸው ጉዳዮች ግን ቡድኑ በወጣቶች እየተገነባ መሆኑና ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ማሳየቱ ነው፡፡ በዚሁ የምንቀጥል ከሆነ በመጪው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጥሩና ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መፍጠር እንችላለን የሚል ተስፋ መያዛችን ለእኔ ደስታ ይሰጠኛል፡፡”

ስለ የቡድን አስተዳደርና የሳቸው የግል ስብዕና

“እኔ በግሌ በኢንስትራክተርነቴ ስልጠናዎችንም ስሰጥ ለአሰልጣኞች ሁሌም የምላቸው በተጫዋችና በአሰልጣኝ መካከል የአባታዊ እና ወንድማዊ ግንኙነት መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ዘመኑም የሚፈቅደው ይህንኑ ነው። እኔ ጠንካራ መሆን የምፈልገው ተጫዋቾቹ ላይ ሳይሆን ሥራው ላይ ነው፡፡ በዚህም ለአንድ ዓመት በዘለቀው ጉዟችን ላይ ምንም አይነት ኮሽታ ሳይኖር መዝለቅ የቻልነው። እንደ ሀዋሳው ዓይነት የዲሲፕሊን ግድፈቶች ሲኖር በተመሳሳይ አሁንም ባህር ዳር ላይ የተከሰቱት ዓይነት አጋጣሚዎች ሲኖሩ የያዝነው ሀገራዊ ሀላፊነት እንደመሆኑ ያለ ርህራሄ እርምጃ እንወስዳለን፡፡”

ስለ ቡድኑ አለመጋጋት

“ከጉዳት ጋር በተያዘ ያጣናቸው ተጫዋቾች አሉ ፤ ነገርግን አንድ ቡድን ተቀየረ የምንለው ከግማሽ በላይ ተጫዋቾች ሲለወጥ ነው። አሁን ላይ ያለው ቡድን ግን 90 በመቶ ያህሉ የነበሩ ተጫዋቾች ናቸው። ስለዚህ አሁንም በሂደት የተወሰኑ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን በመጨመር ጠንካራ ቡድን ለመገንባት እንጥራለን፡፡”

ስለቀጣይ አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅት

“በአመዛኙ በቻን ማጣሪያ ወቅት በያዝነው የቡድን ስብስብ ላይ የተወሰኑ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ጨምረን ልምምድ እንጀምራለን። በእቅዳችን መሠረት ዓርብ ለመጀመር ነበር፤ ነገርግን በአዲሰ አበባ ሲቲ ካፕና በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የተነሳ ቀኑ ወደ መጪው ሰኞ ሊዘዋወር ችሏል፡፡

“ዝግጅታችንን ሰኞ በመቐለ ከተማ የምንጀምር ሲሆን ከፊታችን ያሉት ሁለቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ጥንቃቄ የሚሹ ናቸው። ምክንያቱም የመጀመሪያው ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ሲሆን ሁለተኛውና በሜዳችን የምናደርገው ጨዋታ ደግሞ ያለምንም የማገገሚያ ጊዜ ከጉዞ መልስ በሦስት ቀናት ውስጥ የምናደርገው ስለሚሆን ጨዋታውን ፈታኝ ያደርግብናል። ይህንን ለመቋቋም ይረዳን ዘንድ የተሻለ ቡድን ለመገንባት እንጥራለን ፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ