የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋጫ | ፋሲል ከነማዎች ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ከጉዳት መልስ አግኝተዋል

ዐፄዎቹ ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾችን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ ለጨዋታው የማይደርሱ ተጫዋቾችም ታውቀዋል።

ቀጣይ እሁድ በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ መቐለ 70 እንደርታን የሚገጥሙት ዐፄዎቹ አምበላቸው ያሬድ ባየህ እና ሐብታሙ ተከስተን ከጉዳት መልስ ማግኘት ችለዋል። አዲሶቹ የቡድኑ ፈራሚዎች ጋናዊያኑ ኦሴይ ማውሊ እና ጋብርኤል አሕመድ የቀድሞ ክለባቸው ለመግጠም ዝግጁ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በትናንትናው ዕለት ወደ አዲስ አበባ በማምራት ልምምዳቸው የጀመሩት ዐፄዎቹ ሁለቱ ተጫዋቾችን ቢያገኙም ጀማል ጣሰው፣ ሰለሞን ሃብቴ እንዲሁም አዲስ ፈራሚዎቹ መልካሙ ታውፈር እና ኤፍሬም ክፍሌን በጉዳት ምክንያት በጨዋታው አያገኙም።

ባለፈው የውድድር ዓመት ሀዋሳ ከተማን በፍፁም ቅጣት ምት ረተው የኢትዮጵያ ዋንጫን ያሸነፉት ፋሲሎች ከዚ ቀደም በባህር ዳር የዝግጅት ጊዜያቸው በርካታ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ማድረጋቸው ሲታወስ ቀጣይ እሁድ የሚያደርጉት ጨዋታም ለአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የመጀመርያው የሃገር ውስጥ የነጥብ ጨዋታ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ