በ3ኛው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት ዙሪያ መግለጫ ሲሰጥ የመጨረሻ እጩዎችም ታውቀዋል

ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ በሚደረገው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት ዙሪያ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ብሮካስቲንግ ኮርፓሬሽን ዋና መስሪያ ቤት መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

መግለጫው የኢቲቪ ስፖርትና መዝናኛ ቻናል ኃላፊ የሆኑት አቶ ካሳሁን ቃሲም፣ የጣቢያው ስፖርት ክፍል ም/ኃላፊ የሆነው ጋዜጠኛ ግርማ በቀለ እና የተቋሙ የብራንዲንግና ማርኪቲንግ ኃላፊ አቶ ጋሻው በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

በ2009 ዓ.ም ጠንካራ የፉክክር መንፈስ በመፍጠር በዓለምአቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆኑ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ ኢቢሲ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት በማሰብ በእግርኳስና በአትሌቲክስ የስፖርት ዓይነቶች በአራት ዘርፎች የተጀመረው ሽልማቱ አምና በተመሳሳይ የስፖርት ዓይነቶች ዘርፎችን ወደ አምስት በማሳደግ በሸራተን ሆቴል በተካሄደ መርሃግብር እውቅና መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ዘንድሮም በተመሳሳይ በአምስት ዘርፎች በስፓርት ባለሙያዎች፣ ምሁራንና የስፖርት ጋዜጠኞች በድምሩ ስምንት አባላት ያሉት የቴክኒክ ኮሚቴ በእግርኳስና አትሌቲክስ የስፖርት መስኮች አስር እጩዎች ቀርበው ላለፉት ወራት በአጭር የፅሁፍ መልእክት እና በፌስቡክ ድምፅ ሲያሰባስቡ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡

ከቀረቡት አስር እጩዎች መካከል በሁለቱም የስፖርት መስኮች የመጨረሻ ሦስት እጩዎች ይፋ ተደርገዋል። የመጨረሻዎቹ ሦስት እጩዎች የተለኡበትም ሂደትም 75% ከባለሙያዎች በተሰበሰበ እንዲሁም 25% ከአድማጭ ተመልካቹ በተሰበሰበ ድምፅ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት በሴቶች እግርኳስ እመቤት አዲሱ፣ ሴናፍ ዋቁማ እና ሰናይት ቦጋለ ለመጨረሻ እጩነት ሲቀርቡ በወንዶች ደግሞ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ያሬድ ባየህ የመጨረሻ እጩዎች ሆነዋል፡፡

በመጪው ጥቅምት 29 በስካይ ላይት ሆቴል በደማቅ ሁኔታ በሚካሄደው መርሃግብር አሸናፊዎቹ የሚለዩ ይሆናል። በተያያዘም በዘንድሮ የ3ኛው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት ላይ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በስፓርታዊ ጨዋነት ጥሩ አበርክቶ ለነበራቸው የእውቅና ምስክር ወረቀት የሚበረከት ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ