ከፍተኛ ሊግ | ደቡብ ፖሊስ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ደቡብ ፖሊስ አስቀድሞ በአዲሱ ፎርማት የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑ በመገለፁ በርካታ ተጫዋቾችን አስፈርሞ የነበረ ቢሆንም ኃላ ላይ በከፍተኛ ሊጉ እንዲቀጥል በመወሰኑ ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ ጋር በመለያየት በምትኩ ተጫዋቾችን እየቀላቀለ ይገኛል። በዛሬው ዕለትም ሦስት ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

የመሐል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ጌቱ ባፋ ከፈረሙት መካከል ነው። ጌቱ ከዚህ ቀደም ለሱሉልታ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ኢኮስኮ የተጫወተ ሲሆን ያለፈውን የውድድር ዓመት ደግሞ በስልጤ ወራቤ አሳልፏል።

ሌላኛው የክለቡ አዲስ ተጫዋቹ ወጣቱ ተከላካይ አባተ ዓለሙ ነው፡፡ በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ የታዳጊ ፕሮጀክቶች በመጫወት ያሳለፈው ተጫዋቹ የክለብ ህይወትን ለመጀመር ፖሊሶችን ተቀላቅሏል፡፡

ሦስተኛው ፈራሚ የቀኝ መስመር ተከላካዩ እስራኤል መንግስቱ ነው። ከዚህ ቀደም በወልቂጤ ከተማ ሲጫወት የነበረው እስራኤል የተሰጠውን የሙከራ ጊዜ በመጠቀም አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን በማሳመኑ ፊርማውን አኑሯል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ