ከፍተኛ ሊግ | ሶሎዳ ዓድዋ ሦስት ተጨማሪ ተጫዋቾች አስፈረመ

በዝውውር መስኮቱ በርካታ ተጫዋቾች በማስፈረም ላይ የሚገኙት ሶሎዳ ዓድዋዎች ናይጀርያዊ ግብ ጠባቂ ጨምሮ ሦስት ተጫዋቾች አስፈርመዋል።

ከፈራሚዎቹ አንዱ ከቀናት በፊት ዝውውሩን የጨረሰው አማካዩ ኤርምያስ ብርሃነ ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ከአክሱም ከተማ ጋር ያሳለፈው ተጫዋቹ ለቡድኑ ጥሩ ግብዓት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለተኛው ቡድኑ የተቀላቀለው አንጋፋው ናይጀርያዊ ግብጠባቂ ሰንደይ ሮቲሚ ነው።
ባለፈው የውድድር ዓመት ከበርካታ ዓመታት የሪቨርስ ቆይታው በኋላ ወደ ስሑል ሽረ አምርቶ ቡድኑን በቋሚነት ያገለገለው ይህ ግብጠባቂ ከዚ በፊት ለኢስራኤሎቹ ሃፖል አሽካሎን እና አይሮኒ ሪሾን ዛዮን ጨምሮ ለሃገሩ ሳንሻይን ስታርስ ተጫውቶ አሳልፏል።

ሦስተኛው የቡድኑ ፈራሚ አጥቂው አላዛር ዘውዱ ነው። በበርካታ ቦታዎች መጫወት የሚችለው ይህ ተጫዋች ባለፈው የውድድር ዓመት ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ያሳለፈ ሲሆን በአጥቂነት እና በመስመር ተጫዋችነት መሰለፍ የሚችል ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ