የትግራይ ዋንጫ | የጦና ንቦች ደደቢትን አሸንፈዋል

የትግራይ ዋንጫ ዛሬም ሲቀጥል ወላይታ ድቻ ደደቢትን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፏል።

አሰልቺ እንቅስቃሴ የታየበት እና በሙከራዎች ያልታጀበው ይህ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተጠና አጨዋወት ያልታየበት ነበር። በተለይም በደደቢቶች በኩል በመጀመርያው ጨዋታ የነበሩት ክፍተቶች በዛሬው ጨዋታም በተመሳሳይ ታይተዋል።

በጨዋታው ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ሲሆኑ ሙከራውም በባየ ገዛኸኝ ከረጅም ርቀት የተደረገ ነበር። አጥቂው ከመጀመርያው ሙከራ ብዙም ሳይቆይም ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርጎ ነበር በተለይም ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቶ ዘልአለም ሉቃስ ያዳነበት ኳስ ለግብ የቀረበ ነበር። ወላይታ ድቻዎች በቸርነት ጉግሳ ፣ ባየ ገዛኸኝ እና ይግረማቸው ተስፋዬም ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይም ይግረማቸው ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ዘልአለም ሉቃስ ያዳነው እና ባየ ገዛኸኝ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በአጋማሹ ለብቸኛ አጥቂው ኑሁ ፉሴይኒ በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት የሞከሩት ሰማያዊዎች ምንም እንኳ የተሳካ የማጥቃት አጨዋወት ባይኖራቸውም የተወሰኑ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ቃልኪዳን ዘለአለም ከፉሴይኒ የተላከለት ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ እና በመልሶ ማጥቃት ሄደው ፉሴይኒ ያመከነው የግብ ዕድል ይጠቀሳሉ። ክፍሎም ሐጎስ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቶት መክብብ ደገፉ የመለሰው ሌላ የግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ የወላይታ ድቻዎች ፍፁም ብልጫ የታየበት ነበር። ሆኖም በአጋማሹ ግብ ለማግባት ቀዳሚ የነበሩት ደደቢቶች ነበሩ፤ በወላይታ ድቻ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መነካቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ቃልኪዳን ዘልአለም ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከጎሉ በኃላ አቻ ለመሆን ግዜ ያልወሰደላቸው ወላይታ ድቻዎችም ከሰባት ደቂቃዎች በኃላ አቻ መሆን ችለዋል። አንተነህ ጉግሳ ከመአዝን የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ነበር ግቡን ያስቆጠረው።

ደደቢቶች ከግቡ በኃላ በአፍቅሮት ሰለሞን አማካኝነት አቻ ለመሆን ተቃርበው የነበረ ቢሆንም አማካዩ የመታት ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥታለች።

በሰባ ስምንተኛው ደቂቃም ወላይታ ድቻዎች የጨዋታው መሪ የሆኑበት ግብ አስቆጥረዋል። ግቧም ታምራት ስላስ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ካደረገው ዳንኤል ዳዊት የተላከለት ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ነበር ያስቆጠረው።

ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ወላይታ ድቻዎች ነጥባቸውን ወደ አራት ሲያደርሱ ደደቢቶች ከውድድሩ መሰናበታቸው አረጋግጠዋል።

የጨዋታው ኮከብ የወላይታ ድቻው ዳንኤል ዳዊት በመሆን ተመርጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ