የከፍተኛ ሊግ ዕጣ የሚወጣበት ቀን ሽግሽግ ተደረገበት

የሁለተኛው የሊግ ዕርከን የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት በአራት ቀናት ተራዝሟል።

የ2012 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዕጣ አወጣጥ ሥነስርዓት በመጪው ህዳር 20 ይደረጋል ቢባልም ቀኑ ወደ ህዳር 24 መቀየሩ ታውቋል። ከዕጣ ማውጣት በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ይፋ ከተደረገው የምድብ ድልድል መጠነኛ ለውጦችም እንደሚደረጉም ከውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። ምንጮቹ አያይዘው እንደገለፁት ምድብ ‘ሀ’ በነበረበት ሊቀጥል እንደሚችልና ምድብ ‘ለ’ እና ‘ሐ’ ላይ የተወሰኑ ክለቦች ለውጦች እንደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡ ለውጡ የመጣው የቡድኖቹን የቦታ ርቀት፣ የበጀት አቅም እና ባሳለፍነው ዓመት ያስመዘገቡትን ውጤት ባማከለ መልኩ ሲሆን ከዕጣ ማውጣቱ መርሀ ግብር አስቀድሞ ክለቦቹ በጉዳዩ እንደሚወያዩበት ይጠበቃል።

በተያያዘ ዜናም በአምስት ቡድኖች የተከፈሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ አባላት አዲስ አበባን ሳይጨምር በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ክልሎች በመዘዋወር ከዛሬ ጀምሮ የሜዳ ግምገማ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት “ውሳኔው ዘግይቷል፤ በባለፈው ዓመት ለቡድኖች ደብዳቤ ተልኮ ነበር። ነገር ግን ብዙ ለውጥ አልታየም፤ እኛም ብዙ አልተጫንም ነበር። በዘንድሮ ውድድር ዓመት ግን ለቡድኖቹ በቅድሚያ ደብዳቤ ተልኳል። ከዛም ባለፈ የደሞዝ ጣሪያ ለመወሰን በተሰብሰብነት ወቅት እኔም አስረግጬ በመንገር እነሱም ይህን እንደሚያደርጉ ተማምነን ነበር የተለያየነው።” ብለዋል።

በውድድሩ አንድ ክለብ በሜዳው ጨዋታዎችን ለማድረግ የሚስፈልገው

1. ተመልካችን ከተጫዋቾች ወይም ከቡድን አባላቱ የሚለይ አጥር

2. የተጫዋቾች እና የዳኞች የልብስ መቀየርያ

3. መፀዳጃ ቤት

4. አመቺ የመጫወቻ ሜዳ

ይህን የማይተግብሩ ቡድኖች በቅርብ ርቀት በሚገኝ መስፈርቱን በሚያሟላ ሜዳ ላይ የሚጫወቱም ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ