በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ኮትዲቯር ኒጀርን አሸንፋለች

ኒጀር፣ ኮትዲቯር፣ ኢትዮጵያ እና ማዳጋስካር በሚገኙበት ምድብ በተደረገ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ኮትዲቯር ኒጀርን በሜዳዋ አሸንፋለች። ኢትዮጵያ ደግሞ ጉዞዋን በሽንፈት ጀምራለች።

በኢብራሂም ካማራ የሚሰለጥኑት ዝሆኖቹ በትላንቱን ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ መንቀሳቀሳቸው ታይቷል። በተለይ አሰልጣኙ በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችን በመጠቀም ጨዋታውን እንዳከናወኑ ተስተውሏል። ኢብራሂም ካማራ ከተጠቀሟቸው የመጀመርያ 11 ውስጥ የቶተንሃሙ ሰርጂ ኦሪየር፣ የአርሰናሉ ኒኮላ ፔፔ፣ የቱሉዙ ማክስ አልን ግራድ እና የኤሲ ሚላኑ ፍራን ኬሲ ተጠቃሽ ናቸው።

በጨዋታው ጥሩ ጥሩ የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ የነበሩት ዝሆኖቹ በ68ኛው ደቂቃ በፍራንክ ኬሲ አማካኝነት ባስቆጠሩት የፍፁም ቅጣት ምት ኒጀርን ረተዋል። ቡድኑ ካስቆጠረው የ68ኛ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ውጪ በ23ኛው ደቂቃ ሌላ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቶ የቱሉዙ የመስመር አጥቂ ማክስ አለን ግራድ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ኮትዲቯር ኢትዮጵያን 1-0 ያሸነፈችውን ማዳካስካር በአልፋ ቤት በልጣ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ዋሊያዎቹ የማጣርያ ጉዟቸውን በሽንፈት ጀምረዋል

በማሀማኒሳ ሙኒሲፓል ስታዲየም የተደረገው የማዳጋስካር እና ኢትዮጵያ ጨዋታ በጋባዦቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የነበረችው ማዳጋስካርን ብቸኛ ጎል በ18ኛው ደቂቃ ራያን ራቬልሰን ከማዕዘን ከተሻማ ኳስ አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ጥሩ የተንቀሳቀሰ ሲሆን የተሻሉ የጎል እድሎችን ቢፈጥርም ጎል ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል።

ዝሆኖቹ ሰኞ ባህር ዳር ይገባሉ

ኮትዲቫሮች ማክሰኞ የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ከኢትዮጵያ ጋር ለማከናወን ሰኞ ከሰዓት ባህር ዳር እንደሚገቡ ታውቋል። የዝሆኖቹ 2 አስተባባሪዎች ከትላንት በስትያ ባህር ዳር ገብተዋል። አስተባባሪዎቹ የመጡት ለቡድኑ የተመቸ ማረፊያ ለማመቻቸት እና የብ/ቡድኑን እለታዊ የምግብ ሜኑ ለሚያርፉበት ዊን ሆቴል ለማሳወቅ ነው ተብሏል፡፡

በቻርተር አውሮፕላን ሰኞ እንደሚመጡ የሚጠበቁት ዝሆኖቹ በእለቱ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስቴዲየም ልምምድ እንደሚሰሩ ይጠበቃል። ጨዋታውንም ማክሰኞ 10 ሰዓት ካከናወኑ በኋላ ምሽቱን ከኢትዮጵያ ለመውጣት እንዳቀዱ ሰምተናል።

ዊልፍሬድ ዛሀ በኢትዮጵያው ጨዋታ ዝርዝር ውስጥ ይገኛል

ሶከር ኢትዮጵያ ቡድኑ ከሚያርፍበት ዊን ሆቴል እንዳገኘው መረጃ ከሆነ አስተባባሪዎቹ ለሆቴሉ በሰጡት የቡድን ዝርዝር ውስጥ የክሪስታል ፓላሱ የመስመር ተጨዋች ዊልፍሬድ ዘሃ እንደሚገኝ ተረጋግጧል። ነገር ግን ተጨዋቹ ትላንት ቡድኑ ኒጀርን በገጠመው ስብስብ ሳይካተት ቀርቷል።

የደረጃ ሠንጠረዥ

# ምድብ 11 ተጫ  ልዩ ነጥብ 
1 አይቮሪኮስት 1 +1 3
2 ማዳጋስካር 1 +1 3
3 ኢትዮጵያ 1 -1 0
4 ኒጀር 1 -1 0

© ሶከር ኢትዮጵያ