ሴካፋ ሴቶች ዋንጫ | ሉሲዎቹ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ

የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ትላንት የተጀመረ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ሉሲዎቹ የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

የምድብ አንድ የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ትላንት መከናወን ሲጀመሩ 8:00 ላይ በመክፈቻው መርሀግብር በሁለት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ዋና ዳኛ ፀሀይ እና ረዳቷ ወይንሸት አበራ የተመራው የቡሩንዲ እና ዛንዚባር ጨዋታ በቡሩንዲ 5-0 አሸናፊነት ተደምድሟል። 10:00 ላይ ደግሞ በሁለተኛው ጨዋታ አስተናጋጇ ታንዛኒያ ደቡብ ሱዳንን 9-0 ረምርማለች፡፡ ይህን ጨዋታ በረዳት ዳኝነት ወጋየሁ ዘውዴ መርታዋለች፡፡

የምድብ ለ ሁለት መርሀ ግብሮች ዛሬ ሲጀመሩ ቀን 8:00 ኢትዮጵያ ከኬኒያ በ10:00 ደግሞ ዩጋንዳ ከጅቡቲ ይጫወታሉ፡፡ ወደ ታንዛኒያ ካመሩ ቀናት ያስቆጠሩት ሉሲዎች በጥሩ ሁኔታ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ቆይታቸውም ጥሩ እንደሆነ እና አየሩን ለመልመድ ቀድመው መምጣታቸው እንደጠቀማቸው አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ አሰልጣኙ አክለውም የተሻለ ውጤት ዛሬ ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ እንገባለንም ሲሉ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ሉሲዎቹ ዛሬ ኬኒያን ሲገጥሙ በ4 – 3 – 3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገቡ የመጀመርያ ተሰላፊዎቹም እንደሚከተለው ሆነዋል፡፡

ታሪኳ በርገና

መስከረም ካንኮ – ጥሩአንቺ መንገሻ – ዓለምነሽ ገረመው – ዕፀገነት ብዙነህ

ህይወት ደንጊሶ – ብርቱካን ገብረክርስቶስ (አ) – እመቤት አዲሱ

ሴናፍ ዋቁማ – ረሂማ ዘርጋው – ሽታዬ ሲሳይ


© ሶከር ኢትዮጵያ