የትግራይ ዋንጫ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ሲዳማ ቡና በይገዙ ቦጋለ ብቸኛ ግብ ወላይታ ድቻን በማሸነፍ ሁለተኛው የትግራይ ዋንጫን አንስቷል። 

እንደተጠበቀው እጅግ ማራኪ ፉክክር እና ሳቢ ጨዋታ በታየበት ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ያሳዩበት ቢሆንም በቁጥር የተሻለ ሙከራ በማድረግ ረገድ ግን ወላይታ ድቻዎች የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም በጨዋታው ስድስተኛ ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ በግርግር መሃል ያገኛትን ኳስ አስቆጥሮ ሲዳማን መሪ ማድረግ ችሏል።

በመጀመርያው አጋማሽ የሰመረ የኳስ አመሰራረት ሂደት የነበራቸው እና ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድምያ ሰጥተው የተጫወቱት ሲዳማዎች በተጋጣሚ የሜዳ ክልል በነበራቸው አናሳ የተጫዋቾች ቁጥር እንደሚፈለገው በርካታ ዕድሎች ባይፈጥሩም በይገዙ ቦጋለ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ ዕድሎች ፈጥረው ነበር።

በመጀመርያው አጋማሽ በአመዛኙ በመልሶ ማጥቃት እና በመስመር በሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ተጋጣምያቸው ለማጥቃት የሞከሩት የጦና ንቦች ጥረታቸው ሰምሮ ግብ ባያስቆጥሩም በባየ ገዛኸኝ በሶስት አጋጣሚዎች እና በነጋሽ ታደሰ አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር።
በተለይም ነጋሽ ታደሰ የግብ ጠባቂው መውጣት አይቶ ከርቀት መቷት መሳይ አያኖ እንደምንም ያወጣት ኳስ እና ባዬ ገዛኸኝ በተከላካዮች ስህተት አግኝቶ ያመከናት ወርቃማ ዕድል ይጠቀሳሉ።

እንደመጀመርያው አጋማሽ ሳቢ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ሲመለሱ ጥቂት የማይባሉ ንፁህ ዕድሎችም ፈጥረው ነበር። ከነዚህም ባየ ገዛኸኝ ቸርነት ጉግሳ ከመስመር አሻምቶለት ተጠቅሞ በግምባር ያደረጋት ሙከራ እና ደጉ ደበበ ከማዕዝን የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

በቁጥር ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ ሙከራዎች ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎችም ጨዋታውን በሁለት የግብ ልዩነት መምራት የሚያስችላቸው ዕድሎች ፈጥረው ነበር። ከነዚህም ሃብታሙ ገዛኸኝ ከርቀት አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ እንደምንም ያዳናት ኳስ እና ዮሴፍ ዮሐንስ ከርቀት ያደረጋት ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ጨዋታው በዚ መጠናቀቁ ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች የሁለተኛው ትግራይ ዋንጫ አሸናፊ ሆነዋል። የጨዋታው ኮከብም የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ጊት ጋትኮች ሲሆን ወደ ፍፃሜው የገቡት ሁለቱ ቡድኖችም የሁለት መቶ ሺህ ብር ሽልማት ይበረከትላቸዋል ተብሏል።

ኮከብ ተጫዋች፡ ዳዊት ተፈራ (ሲዳማ ቡና)

ከፍተኛ ግብ አግቢ፡ ዘካርያስ ፍቅሬ (አክሱም ከተማ – 4 ጎሎች)

ኮከብ ግብ ጠባቂ – ሰንደይ ሮትሚ (ሶሎዳ ዓድዋ)

ኮከብ አሰልጣኝ – ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ምስጉን ዋና ዳኛ – አማኑኤል ኃይለሥላሴ

ምስጉን ረዳት ዳኛ – ጥዑማይ ካህሱ


© ሶከር ኢትዮጵያ