የትግራይ ዋንጫ | አክሱም ከተማ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቀቀ

አክሱም ከተማዎች ሶሎዳ ዓድዋን በመለያ ምት በማሸነፍ የትግራይ ዋንጫ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በአክሱም ከተማዎች ብልጫ የጀመረው ጨዋታው ምንም እንኳ በርካታ ሙከራዎች ባይታዩበትም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃም ዘካርያስ ፍቅሬ በሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ ወደ ጎልነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተጋጣምያቸው ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት ሶሎዳ ዓድዋዎች በአስራ አንደኛው ደቂቃ ላይ በኃይልሽ ፀጋይ አማካኝነት በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥረዋል። ፍፁም ቅጣት ምቱ በአክሱም ሳጥን ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠ ነበር።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት ዓድዋዎች ከተጠቀሰው ሙከራ በኃላ ጫና ፈጥረው በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም መሐሪ አድሐኖም ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ እና ኃይልሽ ፀጋይ ብቻው ገብቶ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

በመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የተንቀሳቀሱት አክሱሞች በጨዋታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢኖራቸውም ዘካርያስ ፍቅሬ ከረጅም ርቀት አክርሮ መቷት ሰንደይ ሮትሚ ካዳናት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ወደ ግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ ንፁህ የግብ ዕድሎች የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ የሶሎዳ ዓድዋዎች ብልጫ የታየበት ነበር። በአጋማሹ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩትም ሶሎዳ ዓድዋዎች ሲሆኑ ሙከራውም በሙሉዓለም በየነ አማካኝነት የተደረገ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ መሻሻሎች ያሳዩት ሶሎዳ ዓድዋዎች በሃፍቶም ገብረእግዚአብሔር ፣ እድሪስ ዓብዱልናፊ እና ሃይልሽ ፀጋይ ሶስት ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ሃፍቶም ገብረእግዚአብሔር በጥሩ የጨዋታ ፍሰት የመጣውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ከርቀት የተደረገ ሙከራ እና እድሪስ ዓብዱልናፊ በውሳኔ አሰጣጥ ችግር ያመከነው ኳስ ይጠቀሳሉ።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ወርደው የታዩት አክሱም ከተማዎችም በዘካርያስ ፍቅሬ እና አሸናፊ እንዳለ ጥሩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር በተለይም አሸናፊ እንዳለ ከመአዝን የተሻማው ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር።

መደበኛ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ተከትሎ ጨዋታው ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምቶች አምርቶ አክሱም ከተማዎች አራት ለሁለት አሸንፈዋል። በጨዋታውም የሶሎዳ ዓድዋው ሃፍቶም ገብረእግዚአብሔር ኮከብ ተብሎ ተሸልሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ