የኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርሲቲ በዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ሻምፒዮና ላይ አፍሪካን ይወክላል

በአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ላይ ዋንጫ ማንሳት የቻለው የኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርሲቲ አፍሪካን በመወከል በቻይና አስተናጋጅነት በሚደረግ የዓለም የዩኒቨርሲዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና ላይ ይካፈላል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት ሲደረግ በነበረው የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ከወከሉ ተቋማት መካከል የኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነበር፡፡ ቡድኑ በውድድሩ ላይ በእግር ኳስ የዋንጫ አሸናፊ ሆኖ በማጠናቀቁ አፍሪካን በመወከል በዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ላይ ይሳተፋል፡፡ ከህዳር 11 እስከ 21 በቻይናዋ ንጅያንግ ከተማ ለሚደረገው ለዚህ ውድድር ለበርካታ ቀናት ልምምዱን ሲያደርግ የቆየው ቡድኑ ትላንት ሽኝት ተደርጎለት ወደ ስፍራው ተጉዟል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አዲሱ የውድድር እና ስነስርአት ኮሚቴ ሰብሳቢው ወገኔ ዋልተንጉስ (ዶ/ር) በዩኒቨርሲቲውም በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል የሚሰሩ ሲሆን ቡድኑን በአሰልጣኝነት ይመሩታል፡፡ በአሸኛኘቱ ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በእለቱ በመገኘት “ሀገራዊ አደራን ተረክባችሁ በመጓዛችሁ ኢትዮጵያን እያሰባችሁ ውጤታማ እንድትሆኑ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።” ያሉ ሲሆን ሰንደቅ አለማንም ለቡድኑ በአደራ መልክ አስረክበዋል፡፡

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሀነ መስቀል፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት የበላይ ጠባቂ አቶ ዓባይ በላይነህ የመልካም ምኞት መግለጫን ለቡድኑ አስተላልፈው ቡድኑ ወደስፍራው ትላንት አምርቷል፡፡

የኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርሲቲ ከሜስሲኮ፣ ታይላንድ እና ቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተደልድሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ