አአ ከተማ ዋንጫ | መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ 3ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቀቀ

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎቻቸውን በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሰበታ የተሸነፉት ኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያን አገናኝቶ ጦሩ በመለያ ምቶች በማሸነፍ 3ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል።

ከወትሮው ዝቅ ያለ ተመልካች በተከታተለው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና የኋላ መስመሩን በሦስት ተከላካዮች በማዋቀር የጀመረ ሲሆን በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ምክንያት ያልተጠቀመባቸው አቡበከር ናስር እና ታፈሰ ሰለሞንን አሰልፎ ተጫውቷል።

በዚህ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥርም ሆነ የጎል ዕድል በመፍጠሩ ረገድ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ጎል ለማስቆጠርም ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በ7ኛው ደቂቃ ከታፈሰ ሰለሞን ተሻገረለትን ኳስ አቡበከር ናስር የግብ ክልሉን ለቆ ወጣው ታሪኩ አረዳን በማለፍ ቡናማዎቹን ቀዳሚ አድርጓል።

ከጎሉ በኋላም ኢትዮጵያ ቡና በጥሩ አጀማመሩ ቀጥሎ ተጨማሪ ጎል ሊሆን የሚችል ዕድል አምክኗል። በ11ኛው ደቂቃ በጥሩ ሁኔታ ወደ መከላከያ ጎል ክልል በመቅረብ ታፈሰ ሰለሞን በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ሀብታሙ ታደሰ ያቀብለዋል ተብሎ ሲጠበቅ በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ ግብ ጠባቂው በቀላሉ ተቆጣጥሮታል። በተጨማሪም ከቀኝ መስመር አቡበከር ወደ ጎል የላከውን ኳስ ግብ ጠባቂው ታሪኩ ሲመልሰው በቅርብ ርቀት የነበረው ሀብታሙ በድጋሚ ወደ ጎል መትቶ በተከላካዮች የተመለሰበት ሌላ ወርቃማ አጋጣሚ ነበር።

በመጀመርያው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉት መከላከያዎች ያልተደራጀ እንቅስቃሴ ከማድረጋቸው ባሻገር ወደ ጎል የደረሱባቸው አጋጣሚዎችም እጅግ ጥቂት ነበሩ። በ35ኛው ደቂቃ ከዘነበ የተሻማውን ኳስ ሀብታሙ ወልዴ ሲያመቻችለት ፍቃዱ ዓለሙ ሞክሮ የጨዋታው ኮከብ በረከት አማረ ያዳነበት እንዲሁም በ39ኛው ደቂቃ አልመድ ረሺድ ወደ ኋላ የመለሰው ኳስ በማጠሩ ፍቃዱ በድጋሚ ጥሩ እድል ቢያገኝም በረከት ቀድሞ በመውጣት ያዳነበት ሊጠቀሱ የሚችሉ ሙከራዎች ናቸው።

ከእረፍት መልስ የተጫዋች ቅያሪ በማምረግ መከላከያዎች በእጅጉ ተሻሽለው ሲገቡ ጥሩ ጥሩ የጎል እድሎችን መፍጠር ችለዋል። በ54ኛው ደቂቃም ተቀይሮ በመግባት መልካም እንቅስቃሴ ያደረገው መሐመድ አበራ በሳጥን ውስጥ በኢያሱ ታምሩ በመጠለፉ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ምንተስኖት ከበደ በአግባቡ ተጠቅሞ አቻ መሆን ችለዋል።

ከአቻነት ጎሉ በኋላ መከላከያ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም በግብ ጠባቂው በረከት አማረ ድንቅ ብቃት ጎል ሳይሆኑ ቀርተዋል። በተለይም በ55ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ወደ ጎል መትቶ በረከት ሲመልሰው በድጋሚ ቢመታም ግብ ጠባቂው በድጋሚ የመለሰበት፣ በ74ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ሀብታሙ ከርቀት አክርሮ መትቶ በረከት ሲተፋው ዳዊት ማሞ በድጋሚ ሞክሮ ወ ውጪ የወጣበት ኳሶች ጦረኞቹ ወደ መሪነት ሊሸጋገሩባቸው የሚትሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

በዚህ አጋማሽ ተዳክሞ የገባው ኢትዮጵያ ቡና ይህ ነው የሚባል የጎል ማስቆጠር አጋጣሚ መፍጠር ያልቻለ ሲሆን ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምቶች አምርተዋል። በመለያ ምቶቹም መከላከያዎች የመቷቸውን አራት ኳሶች በሙሉ ሲያስቆጥሩ በቡናዎች በኩል ታፈሰ ሰለሞን እና ሬድዋን ናስር አምክነው በመከላከያ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ መከላከያ በውድድሩ 3ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቁ የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆን በረከት አማረ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ