ሎዛ አበራ በአቋም መለኪያ ጨዋታ ግብ አስቆጠረች

በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ለማልታው ቢርኪርካራ ፊርማዋን በማኖር ከቡድኑ ጋር የተሳካ ግዜ በማሳለፍ የምትገኘው ሎዛ አበራ በትናንትናው ዕለት ቡድኗ ቢርኪርካራ በአቋም መለኪያ ጨዋታ ኮርክ ሲቲን በገጠመበት ጨዋታ ግብ አስቆጠረች።

3-3 በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ ሎዛ በሃምሳ ሦስተኛው ደቂቃ ግብ ስታስቆጥር የተቀሩት ሁለት ግቦች በካሊ ዊልስ እና ራይና ጉስቲ አማካኝነት የተቆጠሩ ናቸው።

በዕረፍት ላይ የነበረው የማልታ ሴቶች ሊግ ከሁለት ቀናት በኋላ ሲጀምር በመርሃ ግብሩ መሰረትም ቢርኪርካራ ወደ ቻርለስ አቤላ ስታዲየም በማቅናት አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሞስታን የሚገጥም ይሆናል።

ከማጋር እና ስዌቂ በእኩል አስር ነጥብ ሊጉን እየመሩ የሚገኙት ቢርኪርካራዎች በቀጣይ በሊግ ጨዋታ ከሞስታ፣ ራይደርስ እና ሄበርንያንስ በሱፐር ካፕ ደግሞ ከማግር ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ