ሴካፋ ሴቶች ዋንጫ | ታንዛንያ እና ኬንያ ለፍፃሜ አልፈዋል

በሁለት ምድብ ተከፍሎ ባለፉት ዘጠኝ ቀናት በታንዛኒያዋ ዋና ከተማ ዳሬሰላም ሲደረግ የነበረው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ዛሬ በተደረጉ ሁለት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ተደርገው ለፍፃሜ ያለፉ ሀገራትን ለይቷል፡፡

ቀን 8:00 ከምድብ አንድ የበላይ የሆነችው ኬንያን ከምድብ ሁለት ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀችው ብሩንዲን አገናኝቶ በኬኒያ 5ለ0 የበላይነት ተደምድሟል፡፡ ጀንትሪክ ሺካንጉዋ ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር ዶክራስ ሺኮቤ፣ ማዋሀሊማ አዳም እና ቪቪያን ኮራዞን እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ግቦችን አስቆጥረው ኬንያን ለፍፃሜ እንድታልፍ አድርገዋል፡፡

ቀጥሎ 10:30 ላይ አስተናጋጇ ታንዛኒያን ከዩጋንዳ አገናኝቶ በታንዛኒያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ጠንካራ ፉክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ በመጨረሻ የጭማሪ ደቂቃ አምበሏ አሻ ራሺድ ታንዛኒያን ወደ ፍፃሜ ያሸጋገረችዋን ብቸኛ ኳስ ከመረብ አሳርፋለች፡፡

ከነገ በስቲያ ታንዛንያ ከ ኬኒያ ለዋንጫ ሲፋለሙ ቡሩንዲ ከ ኡጋንዳ ለደረጃ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የነበረች ሲሆን ከምድቡ ማለፍ ሳትችል በመቅረቷ የቡድን አባላቱ ዛሬ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ