ሁለቱ የዋልያዎቹ የኋላ ደጀኖች ለሳምንታት ከጨዋታ ይርቃሉ

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባደረጋቸው ጨዋታዎች ጥሩ የመከላከል ጥምረት ማሳየት የቻሉት ሁለት የመሐል ተከላካዮች ለሳምንታት ከሜዳ ይርቃሉ።

ትናንት በተጠናቀቀው የአአ ከተማ ዋንጫ ለፈረሰኞቹ የ2012 የውድድር ዘመን ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደረገው አስቻለው ታመነ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ባጋጠመው የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት በምንተስኖት አዳነ ተቀይሮ መውጣቱ ይታወቃል። ጉዳቱ በቂ እረፍት የሚያስፈልገው መሆኑን ተከትሎ ከሦስት እስከ አራት ሳምንት ከሜዳ እንደሚርቅም ተሰምቷል። ይህን ተከትሎ አስቻለው የፕሪምየር ሊጉ የመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ሊያመልጡት እንደሚችሉ ታውቋል።

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከማዳጋስካር እና ኮትዲቯር ጨዋታ ላይ ጥሩ ብቃቱን ያሳየው አንተነህ ተስፋዬ በባህር ዳሩ ጨዋታ ወቅት በ66ኛው ደቂቃ እግሩ ላይ ጋጠመው ጉዳት በደስታ ደሙ ተቀይሮ መውጣቱ ይታወሳል። ለአዲስ አዳጊው ሰበታ ከተማ ፊርማውን ያኖረው አንተነህ በአአ ከተማ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ይሰለፋል ተብሎ ቢጠበቅም ባጋጣመው ጉዳት በቀጣይ ከሦስት እስከ አራት ሳምንት ከሜዳ እንደሚርቅ ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ