ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ከውድድር ዓመቱ የመክፈቻ ጨዋታዎች መካከል በሀዋሳ ከተማ የሚደረገውን የሀዋሳ እና ድሬዳዋ ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

በወጣቶች የተገነባውና በዝውውር ገበያው እምብዛም ተሳትፎ ያላደረገው ሀዋሳ ከተማ በአዳማ ከተማ ዋንጫ በነበረው ቆይታ ለመከላከል እጅጉን ቅድሚያ የሚሰጥ ቡድን ስለመሆኑ ፍንጮች ታይተዋል። ለዚህም እንደ ማሳያነት ተስፋዬ መላኩና ዳንኤል ደርቤ የመሰሉ ተጫዋቾችን ቡድኑ በአማካይ ስፍራ ሲጠቀም ተስተውሏል። ከጨዋታዎች ጅማሮ እስከ ፍፃሜ ድረስ በተሻለ ትኩረት ተደራጅተው ለመከላከል ጥረት ያደርጋሉ።

ቡድኑ በወጣቶች መገንባቱ ከሰጠው ጥቅሞች አንዱ ቡድኑ ኳስ በእግራቸው ሲገባ በፍጥነት በቁጥር በርከት ብለው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የተሻለ የአካል ብቃት ዝግጁነት መገኘታቸው ነው። የነገው ጨዋታም በሜዳቸው እንደመሆኑም ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል በመድረስ ተደጋጋሚ የግብ እድል ለመፍጠር አልመው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

የግራ መስመር ተከላካዩ ጌትነት ቶማስ እና ወጣቱ አቤኔዘር ካሣ በጉዳት ለቡድኑ አገልግሎት የማይሰጡ ሲሆን አላዛር መርኔ ዐምና በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ደደቢትን ሲገጥም በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክንያት ጨዋታው ያመልጠዋል።

በክረምቱ በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ያጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በምትካቸው ጥቂት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን እና በርካታ ወጣቶችን ያስፈረሙ ሲሆን አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይንም በቋሚነት አስቀጥለዋል። ሆኖም ከባድ የውድድር ዘመን ሊያሳልፉ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጠ የቅድመ ውድድር ጊዜ አሳልፈዋል። በአዳማ ከተማ ዋንጫ የተሳፉት ድሬዎች በሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደው በጊዜ እንደመሰናበታቸው የውድድር ዘመኑ ዋነኛ አቀራረባቸው ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አዳጋች ነው። ያም ሆኖ ባለፈው የውድድር ዓመት እንደተስተዋለው ቡድኑ ከሜዳው ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ለራሱ የግብ ክልል ተጠግቶ በመጫወት የመልሶ ማጥቃትን ዋንኛ እቅዱ አድርጎ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የሆኑት አምበሉ ሳምሶን አሰፋ እና ረመዳን ናስር በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ከዐምና በተላለፈ ቅጣት ቡድኑን አይመሩም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 16 ጊዜ ሲገናኙ እኩል አምስት አምስት ጊዜ ተሸናንፈው በቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ድሬዳዋ ከተማ 16 ጎሎች በማስቆጠር ብልጫ ሲኖረው ሀዋሳ ከተማ 14 ጎሎችን አስቆጥሯል።

– ሀዋሳ ላይ ባደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች ሀዋሳ ስድስቱን በድል ሲወጣ ድሬ ሁለቱን አሸንፏል። ዐምና በዚህ ሜዳ ባደረጉት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 1-0 ማሸነፉ ይታወሳል።

– በአዳማ ከተማ ዋንጫ ላይ ሁለቱ ቡድኖች በአንድ ምድብ ተደልድለው ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ 

ሀዋሳ ከተማ (4-2-3-1)

ቤሊንጌ ኢኖህ

ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – ኦሊቨር ኩዋሜ

አለልኝ አዘነ – ዘላለም ኢሳይያስ

ብሩክ በየነ – ቸርነት አውሽ – ብርሀኑ በቀለ

መስፍን ታፈሰ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ፍሬው ጌታሁን

ፍሬዘር ካሣ – በረከት ሳሙኤል – ዘሪሁን አንሼቦ – አማረ በቀለ

ያሬድ ታደሰ – አማኑኤል ተሾመ – ፍሬድ ሙሸንዲ – ያሬድ ሀሰን

ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ሳሙኤል ዘሪሁን


© ሶከር ኢትዮጵያ