ፕሪሚየር ሊግ ፡ አዳማ ከተማ ወደ መሪነት ሲመለስ መከላከያ ደረጃውን በከፍተኛ ደረጃ አሻሽሏል

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሄደው አዳማ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና አቻ ተለያይቶ ወደ መሪነት ተመልሷል፡፡ መከላከያም ድል ቀንቶታል፡፡

በ9፡00 አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 1-1 አቻ ተለያይቷል፡፡ በርካታ ቢጫ ካርዶች ባስተናገደውና ውጥረት በነገሰበት ጨዋታ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ሲዳማ ቡናዎች ሲሆኑ ኬንያዊው ኤሪክ ሙራንዳ በ7ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡ ከግቧ መቆጠር 2 ደቂቃዎች በኋላ የመስመር ተከላካዩ ዘነበ ከበደ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ሲዳማ ቡናም ቀሪውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ10 ተጫዋች ለመጫወት ተገዷል፡፡

በ56ኛው ደቂቃ በሲዳማ ቡና የግብ ክልል የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ታፈሰ ተደስፋዬ ወደ ግብነት ቀይሮ አዳማን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ ታፈሰ በውድድር ዘመኑ ያስቆጠረውን ግብ ብዛት 7 ያደረሰ ሲሆን የከፍተኛ ግብ አግቢነቱንም ለብቻው መምራት ችሏል፡፡

በጨዋታው አርቢቴር ሚካኤል አርአያ ለሲዳማ ቡናው ሳውሬል ኦልሪሽ ቢጫ ካርድ ለማሳየት በስህተት ቀይ ካርድ መምዘዛቸው በስፍራው የተገኘውን ተመልካች አዝናንቷል፡፡ የሲዳማ ቡናው የመስመር አጥቂ አዲስ ግደይ ያሳየው አስደናቂ እንቅስቃሴም የባለሜዳውን ቡድን ደጋፊዎች ሳይቀር አድናቆት እንዲለግሱት አስገድዷል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ በ20 ነጥብ የሊጉን መሪነት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሲረከብ ሲዳማ ቡና በ13 ነጥብ ደረጃውን ወደ 3ኛ ከፍ አድርጓል፡፡

በ11፡30 ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው መከላከያ 2-0 አሸንፏል፡፡ በቀዝቃዛማው የአአ ስታድየም የተደረገው ጨዋታ እንደአየር ንብረቱ ሁሉ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን የመከላከያን ቀዳሚ ግብ ከመረብ ያሳረፈው ባዬ ገዛኸኝ ጨዋታው በተጀመረ ገና በ6ኛው ደቂቃ ነው፡፡ በቻን የኢትዮጵያን የአጥቂ መስመር የመራው ሙሉአለም ጥላሁን በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በመግባት በ75ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሸገረውን ኳስ ተጠቅሞ የመከላካያን 2ኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጦሩ ድሉን ተከትሎ 6 ደረጃዎችን አሻሽሎ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ድሬዳዋ ከተማ ሶስት ደረጃ አሽቆልቁሎ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-

wsss

የከፍተኛ ግብ አግቢዎች ደረጃ

Untitled

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *