ሪፖርት| ወልቂጤ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተዋል

በታሪክ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታቸውን ያከናወኑት ወልቂጤ ከተማዎች ሜዳቸው ግንባታ ላይ በመሆኑ ዝዋይ በሚገኘው ሼር ሜዳ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግደው ያለግብ ተለያይተዋል።

በምክትል አሰልጣኝነት እና ተጫዋችነት ቡድኑን እያገለገለ የሚገኘው አዳነ ግርማ በዛሬው ጨዋታ በወልቂጤዎች በኩል በመጀመሪያ ተሰላፊነት ጨዋታውን መጀመር ችሏል፡፡

ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ማጥቃትን የመጀመሪያ ምርጫቸው አድርገው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ግብ ባልተቆጠረበት አጋማሽም ለግብ የቀረበ ሙከራ በማድረግ ቅድሚያውን የወሰዱት ወልቂጤዎች ሲሆኑ ምንተስኖት አዳነ መሀመድ ሁሴን አክርሮ የመታውን ኳስ እንደምንም ብሎ ያወጣበት እንዲሁም 32ኛው እና 43ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ቦታ ላይ በተሰራ ጥፋት ከተገኙት የቅጣት ምቶች አዳነ ግርማ ያደረጋቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በተቃራኒው ጊዮርጊሶች ለግብ የቀረበ ሙከራ ባያደርጉም ከርቀት በቀጥታ አክርረው በሚመቷቸው ኳሶች የወልቂጤዎችን ግብ ክልል ለመፈተሽ የሙከሩ ሲሆን በተለይም በ26ኛው ደቂቃ አቤል ከርቀት የመታት ኳስ የወልቂጤ ተከላካዮች ስህተት ታክሎባት አቅጣጫዋን ስታ ግብ ለመሆን ብትቃረብም ሶሆሆ ሜንሳህ እንደምንም ሊያወጣት ችሏል።

ክፍት በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተሽለው የቀረቡ ቢሆንም የተሻለ የግብ ዕድል በመፍጠር ግን ወልቂጤዎች የተሻሉ ነበሩ። በጊዮርጊሶች በኩል በ58ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም መሀመድ ካሻማው ኳስ አቡበከር ሳኒ ቡድኑን መሪ ሊያደርግ የሚችልበትን አጋጣሚ ሲያመክን በ65ኛው እና በ70ኛው ደቂቃ ደግሞ በአቤል ያለው አማካኝነት የተገኙትን ዕድሎች ሶሆሆ ሜንሳህ በአስደናቂ ሁኔታ ሊያድናቸው ችሏል፡፡ በአንፃሩ ወልቂጤዎች በ60ኛው እና በ81ኛው ደቂቃ ግሩም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኙ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ተመጣጣኝ የቡድን እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ ወደ ሜዳ ተቀይሮ የገቡት ጋዲሳ መብራቴ እና ሀይደር ሸረፋ የቅዱስ ጊዮርጊስን እንቅስቃሴ በማፍጠንም ሆነ የግብ ዕድል በመፍጠር የተሻለ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ ሲሆን በተቃራኒው ወልቂጤዎች አዳነ ግርማን ካስወጡ በኋላ ቡድኑ ሚዛናዊነቱን አጥቶ ታይቷል።

በግራ በኩል ብልጫ የተወሰዳባቸው ወልቂጤዎች ሙሀጅርን በማስገባት የግራ መስመሩን የጥቃት እንቅስቃሴ ለመቋቋም ጥረት ያደረጉ ሲሆን በተለይም የጨዋታ መጠናቀቂያ ላይ ፈረሰኞቹ ተጭነው መጫወት ቢችሉም የአሸናፊነት ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።

ውጤቱም ለወልቂጤ ከተማ በታሪክ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ነጥብ ሆኖ ተመዝግቧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ