“ዘንድሮ የኮከብ ተጫዋች ወይም አስቆጣሪነት ክብርን አልማለሁ” – ሰመረ ሃፍታይ

በዓዲግራቱ ኬኤምኤስ ፕሮጀክት የጀመረው የእግርኳስ ህይወት ለሶስት ዓመታት በወልዋሎ ቢ ቡድን እንዲሁም ካሳለፍነው የውድድር ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ በዋናው ቡድን ላይ እስከመጫወት አድርሶታል። ተስፈኛው ሰመረ ሃፍታይ!

በፕሮጀክት ቆይታው በፊት አጥቂነት ይጫወት የነበረው ሰመረ አሁን ደግሞ በመስመር አጥቂነት እንዲሁም በመስመር ተከላካይነት መጫወት ይችላል።

በ14ኛው የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ በተሰለፈባቸው አጋጣሚዎች ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ተጫዋቹ ትላንት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ክለቡ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሜዳው ውጭ ሰበታ ከተማን 3ለ1 በረታበት ጨዋታ በኹለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት ኹለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

በጨዋታው እንዲሁም በእግርኳስ ህይወቱ ዙሪያ ተከታዩን ቆይታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አድርጓል።



ስለትላንቱ ጨዋታ

“ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር ፤ በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ላይ አስቀድመን ተገናኝተን ስለነበር በደንብ አውቀናቸው ተዘጋጅተን ነበር የቀረብነው። ጨዋታው ከሜዳችን ውጭም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ትንሽ ከብዶን ነበር። ነገር ግን ጨዋታውን አሸንፈን መውጣት ችለናል።”

በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ግብ ማስቆጠሩ ስለፈጠረበት ደስታ

“በፕሪምየር ሊጉ ዐምና በመጨረሻው ሳምንት ከአዳማ ጋር ስንጫወት ተቀይሬ በመግባት የመጀመሪያ የሊግ ግቤን ማስቆጠር ችያለሁ፤ ስሜቴ በጣም የተለየ ነበር። እነዚህን አጋጣሚዎች ልጅም ሆኜ እመኛቸው የነበሩ ናቸው። ከልጅነቴ ጀምሮ ለወልዋሎ ተጫዋች ሆኜ ነጥቦችን እንዲያሳካ እና ዋንጫ እንዲያነሳ ቡድኑን ማገዝ ህልሜ ነበር፤ በዚህ ፍጥነት ህልሜ ተሳክቶ በማየቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።”

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ስለቡድናቸውና ስለግል ዕቅዱ

“እንደቡድን አቅደን እየተንቀሳቀስን የምንገኘው ከአንድ እስከ ሦስት ባለው ደረጃ ውስጥ ለማጠናቀቅ ነው። እኔ በግሌ ደግሞ በሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ወይም ኮከብ ተጫዋች ሆኜ ለመጨረስ አልማለሁ። በተጨማሪም ሀገሬን ወክዬ ለመጫወት ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ።”

በልጅነቱ ያደንቀው ስለነበረው ተጫዋች

“እግርኳስን ስጀምር በፊት አጥቂነት ነበር የጀመርኩት። ከዛም በጊዜ ሄደት በመስመር አጥቂነትና በመስመር ተከላካይ ተጫዋች የሆንኩት። ከልጅነቴ ጀምሮ ጌታነህ ከበደ ሲጫወት ማየት ያስደስተኛል፤ እንደሱ ጨራሽ አጥቂ የመሆንም ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ።”

አሁን አሁን አሰልጣኞች ወጣት ተጫዋቾች ወደ ክለቦች የሚመለምሉት ተጫዋቾቹ ክለቡ የሚገኝበት አካባቢ ተወላጅ ስለሆኑ ከውጪያዊ አካላት በሚመጣ ግፊት እንጂ በአቅማቸው ላይ ተመስርቶ አይደለም እየተባለ ስለሚቀርበው ወቀሳ

“ይህ የተሳሳተ አባባል ነው፤ ዕውነታው እንደዛ አይደለም። ማናችንም ብንሆን ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ከመጡ ተጫዋቾች እኩል ዕድል ተሰጥቶን የተሻልን ከሆንን ዕድሉን እናገኛለን፤ ካልሆነ እንቀነሳለን። ከግሌ ተሞክሮ ስነግርህ እኛ ስንሞክር ብዙ ተጫዋቾች ሆነን ነበር፤ ማሳመን የቻልነው ቀርተናል፤ ሌሎች ደግሞ የሚቀራቸው ነገር ስለነበረ ተመልሰዋል። በአቅማችን እንጂ በጫና አይደለም።”

ስለአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ

“ዮሐንስ ሳህሌ ከሌሎች አሰልጣኞች የተለየ ነው። እሱ በሥራ የሚያምን ሰው ነው፤ የሚሰራ ሰውን እና ወጣቶችን በጣም አድርጎ ይወዳል። ከሌሎች አሰልጣኞች በተለየ ደፋርና በራሱ የሚተማመን አሰልጣኝ ነው፤ በስብስቡ በያዛቸው ተጫዋቾች ከፍተኛ እምነት አለው። በሚሰጠው ስልጠና የተጫዋቾችን አቅም ማሰደግ የሚችል ጠንካራ አሰልጣኝ ነው።

“የዮሐንስ አካሄድ ለሌሎች ክለቦችም ተምሳሌት የሚሆን ነው፤ ሌሎች አሰልጣኞችም በወጣቶች ላይ እምነት በመጣል የተሻለ ነገር ለመስራት መጣር ይኖርባቸዋል።”

ስለቀጣይ ዕቅዱ

“ዘንድሮ በሊጉ ዋነኛ ግቤ ከቡድኔ ጋር ውጤታማ ጊዜ በማሳለፍ ኮከብ ተጫዋች ወይም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ መጨረስ ነው። ወልዋሎ በልቤ የተለየ ቦታ ያለው ክለብ ነው። በተጨማሪም ወደፊት ዕድሉን ባገኝ በኢትዮጵያ ቡና የመጫወት ፍላጎት አለኝ።”

ለሌሎች ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች መልዕክት

“ወጣት ተጫዋች ስትሆን ድንገት በሚመጡ ሙገሳና አድናቆት መንገዳችንን መሳት የለብንም። የሚመጡልን አድናቆቶችን ለቀጣይ ጠንካራ ስራዎች መነሻ አድርገን መጠቀም ይኖርብናል። እንደዛም ሲሆን ነው ከምንፈልገው ግብ መድረስ የምንችለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ