ፋሲል ከነማ በ2011 ቃል የገባውን ስጦታ ለተጫዋቾቹ አበርክቷል

ፋሲል ከነማ ባለፈው ሳምንት የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ላነሳው ቡድኑ በሄርፋዚ ሆቴል ሽልመመት አበርክቷል።

በ2011 የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች በፕሪምየር ሊጉ ላሳዩት ጥሩ ፉክክር እንዲሁም የጥሎ ማለፍ ቻምፒዮን በመሆናቸው የማበረታቻ ሽልማት ቃል የተገባላቸው ቢሆንም በበጀት እጥረት ምክንያት ዘግይቶ ቆይቷል። ቡድኑ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ መቐለ 70 እንደርታን በመርታት አሸናፊ መሆን የቻሉ ሲሆን አጋጣሚውን በመጠቀምም ባለፈው ዓመት ቃል የተገባውን ስጦታ አበርክተዋል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር አዳማ ላይ አከናውነው ወደ ጎንደር ያቀኑት የዐፄዎቹ ተጫዋቾች ከጎንደር አፄ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ጀምረው በደጋፊዎች በመታጀብ ወደ ጎንደር ከተማ የገቡ ሲሆን አመሻሹ ላይ በሄርፋዚ ሪዞርት የእራት ግብዣ ተደርጎላቸዋል።

በሥነስርዓቱ ላይ በርካታ ታላላቅ እንግዶች የተገኙ ሲሆን የክለቡ የልብ ደጋፊዎች እና የቦርድ አባላት የተስፋ እና የሴት ብድን አባላት በፕሮግራሙ ላይ ተጋብዘው ነበር ።

በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ብርሀኑ በ2011 ለፋሲል ከተማ ድጋፍ ያደረጉ በርካታ አጋር ድረጅቶችን አመስግነው ለፋሲል ከነማ ድጋፍ ላደረጉ አካላት በሙሉ ክለብ የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

ከሥራ አስኪያጁ በመቀጠል የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ጋሻው ለደጋፊዎቹ እንዲሁም ለተጫዋቾች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በ2011 የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ደጋፊ ማኅበር ከተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘርፎች 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ለክለብ እንዳስገኙ በመግለፅ በቀጣይ ወደ 10 ሚሊዮን ለማሳደግ እንደሚጥሩ እና ደጋፊዎች ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

በመቀጠልም በክለብ የበላይ የቦርድ ሰብሳቢ እና የጎንደር ከተማ ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ሥዩም አማካኝነት በ2011 ፋሲል ከነማን ላገለገሉ አሰልጣኝ ቡድን አባላት እንዲሁም ለሙሉ የተጫዋቾች አባላት በየደረጀው የገንዘብ ሽልማት ያደረጉ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ 40ሺህ ፣ሁለተኛ ደረጃ 30ሺህ፣ ሶስተኛ ደረጃ 20ሺህ ፣ አራተኛ ደረጃ 10ሺህ ብር ሽልማት ክለቡ አበርክቷል ።

የክለብ የደጋፊዎች ማህበር የምንግዜም አጋራቸው ለሆነው ዳሽን ቢራ የምስጋና ስጦታ ያበረከቱ ሲሆን በመጨረሻም የክለብ ዋና አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እና አምበሉ ያሬድ ባየ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ለከተማው ከንቲባ አስረክበዋል። የፕሮግራሙ መዝጊያ በሄርፋዚ ሪዞርት የተዘጋጀ ኬክ በአሰልጣኝ ስ.ሥዩም ከበደ እና የከተማው ከንቲባ ማስተዋል ስዩም በጋራ በመሆን በመቁረስ ፕሮግራሙን ቋጭተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ