የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 3-2 መቐለ 70 እንደርታ

በፕሪምየር ሊጉ ኹለተኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል ባህር ዳር ላይ የተደረገውን ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ መቐለ 70 እንደርታን 3-2 ካሸነፈ በኋላ አሰልጣኞቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“በመጀመሪያ የሜዳ ላይ ጨዋታዬ ደጋፊዎቻችን በክብር ከስታዲየም እንዲወጡ የነበረኝ ፍላጎት በመሳካቱ በጣም ደስ ብሎኛል” ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

የጨዋታውን እንቅስቃሴ እንዴት አገኘኸው?

በቅድምያ የመጀመሪያ የሜዳችን ላይ ጨዋታችን እንደመሆኑ በስታዲየም የነበረውን ደጋፊ የሚያስደስት ውጤት ማምጣት ነበረብን። ይህ ደግሞ ተሳክቶልናል። ወደ ጨዋታው ስሄድ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጎል ብናገኝም ወደ ተጋጣሚያችን የግብ ክልል ሄደን ማስከፈት ተስኖን ነበረ። ይህንን ችግር በሁለተኛው አጋማሽ ለማስተካከል ሞክረናል። ከዚህ በተጨማሪ በሁለተኛው አጋማሽ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች ተጨዋቾቼ ላይ የትኩረት ማነስ ችግር ተመልክቻለሁ። ይህንን ደግሞ ማሻሻል ይጠበቅብናል።

ቡድኑ ላይ ስለነበሩ መሻሻሎች (ከመጀመሪያው ጨዋታ አንፃር)

በመጀመሪያው ጨዋታ ሶስት ነጥብ የምናገኝበትን እድል አበላሽተናል። ያንን ላለመድገም በልምምድ ላይ ስራዎችን ሰርተን ለዛሬው ጨዋታ ቀርበናል። ጎሎችን የምናገኝበትን መንገድ አቅደን ነበረ የመጣነው። ይህም ደግሞ ተሳክቶልናል።

ስለ ቡድኑ ደካማ ጎኖች

ሙሉ ለሙሉ እንደምንፈልገው እየተጫወትን ነበር ባልልም ባሰብነው መልኩ ጨዋታውን ጀምረናል፣ ጎሎችንም አግኝተናል። ነገር ግን በጨዋታው ብዙ ክፍተቶች ነበሩብን። በተለይ የመልሶ ማጥቃትን የምንከላከልበት ዜዴ ደካማ ነበረ። ከዚህ በተጨማሪ በሁለተኛው አጋማሽ ለተጋጣሚያችን ኳሶችን ማንሸራሸሪያ ቦታዎችን ሰተን ነበረ። ይህንን ወደ ፊት እናርማለን። በአጠቃላይ ግን ተጨዋቾቼ ባሳዩት ነገር ደስተኛ ነኝ።

በስታዲየም ስለተገኘው ደጋፊ

በመጀመሪያ የሜዳ ላይ ጨዋታዬ ደጋፊዎቻችን በክብር ከስታዲየም እንዲወጡ እፈልግ ነበር። ይህ ደግሞ በመሳካቱ በጣም ደስ ብሎኛል።

ስለ ተጋጣሚ ቡድን

መቐለ የዓምና አሸናፊ ቡድን ነው። በእኔ እምነት ጎበዝ አሰልጣኝ አላቸው። ቡድኑም እንደ ቡድን ጠንካራ ቡድን ነው። ከምንም በላይ ቡድኑ የዓምና አሸናፊ እንደመሆኑ የማሸነፍ ስነ ልቦና ወደዚህ ይዘው መተው ከባድ ነገሮችን እንደሚፈጥሩ አስበን ቀድመን ውይይቶችን አድርገናል። ቢሆንም ግን የነሱን ጠንካራ ጎን ሰብረን የራሳችንን አጨዋወት በመተግበር ጨዋታውን አሸንፈናል። ቢሆንም ግን ቡድኔ ብዙ ክፍተቶች ነበሩበት ክፍተቶችን ለማረም በቀጣይ እንሰራለን።

“ቡድኔ ቡድን አይመስልም ነበር፤ ባህር ዳሮች ማሸነፍ ይገባቸዋል።” ገብረመድህን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

በአጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነበር። ነገር ግን ለእኛ ጥሩ የሚባል ነገር ይዞ አልምጣም። በዛሬው ጨዋታ የተከላካይ መስመራችን ከሚገባው በላይ ተዳክሞ ታይቷል። ከነበረው ነገር አንፃር መሸነፍ አይበዛብንም። ባህር ዳሮች ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮም ጎል አስቆጥረውብን ብልጫ ወስደውብናል። ስለዚህ ከነበረው ብልጫ አንፃር ማሸነፍ ይገባቸዋል። እነሱንም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።

ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ስለተወሰደበት ጉዳይ

ይህ ለእኔም አልገባኝም። ተከላካዮቼ ለምን ተረጋግተው እንዳልተጫወቱ ገርሞኛል። ጨዋታው ክፍት ነበር፤ ግን እኛ አልተጠቀምንበትም። በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተጋጣሚያችንን ክፍተት መጠቀም ተስኖን ነበረ። ይህ ደግሞ ዋጋ አስከፍሎናል።

ወደ ሜዳ ይዘውት ስለገቡት እቅድ

እውነት ለመናገር ቡድኔ ዛሬ ምንም የሚገለፅ ነገር አልነበረውም። ቡድኔ ቡድን አይመስልም ነበር። ግብ ከተቆጠረብንም በኋላ መልሰን ግብ ስናስቆጥር የነበሩት ነገሮች በእውቀት የተመሰረቱ አይመስሉም ነበረ። በአጠቃላይ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ አላደረግንም።

በስታዲየም ስለነበረው ድባብ

በጨዋታው ያገኘነው ትልቁ ነገር የደጋፊዎች ሠላማዊ መሆንን ነው። በውጤቱ ብንከፋም በስታዲየም በነበረው ነገር ደስተኞች ነን። በሁለቱ ክለቦች መካከል ፍቅሩ፣ አንድነቱ እና መከባበሩ መምጣቱ በጣም ጥሩ ነው። ግለሰቦች እየተነሱ የሚፅፉት ነገር መሰረተ ቢስ መሆኑ እና ሁለቱን ክልሎች የሚያጋጭ ነገር እንደሌለ ያሳይል። ዛሬ የታየው ነገር መቀጠል አለበት። እነሱ ዛሬ በጥሩ ሁኔታ ተቀብለውን ሸኝተውናል። እኛ ደግሞ ሲመጡ በእጥፍ አድርገን እንመልሳለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ