የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 4-1 ስሑል ሽረ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ዛሬ በብቸኝነት በሲዳማ ቡና እና ስሑል ሽረ መካከል ተደርጎ ሲዳማ ቡና 4ለ1 ከረታ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ድህረ አስታያየት ሰጥተዋል፡፡

“የአጨዋወት መንገዳችንን በመቀየር ውጤታማ ሆነናል” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ ነው። ሁለት ነገር ነበረው፤ የመጀመሪያው አርባ አምስት ላይ ኳስ ይዘን ለመጫወት ሞክረናል። እነሱም በይበልጥ ጎላቸውን ዘግተው ነበር የሚጫወቱት እና በሚመጡ መልሶ ማጥቃቶች ትንሽ አስቸግረውን ነበር፤ ፈትነውንም ነበር። ያንን ነገር ተቆጣጥረን ወጥተናል ግን አቻ ነበር የመጀመሪያ አርባአምስቱ ያለቀው ከእረፍት በፊት የነበረው ተመጣጣኝ ነበር፡፡ ከእረፍት በኃላ ግን ልጆችንም ቀይረን የአጨዋወት መንገዳችንንም በመቀየር ውጤታማ ሆነናል እና ከእረፍት በኃላ የተሻልን ነበርን፡፡

በተከላካይ ስህተት ስለተቆጠረችው ግብ እና የሀብታሙ ገዛኸኝ ተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ መሆን

“ለማሸነፍ ካለን ጉጉት የተነሳ ነው ሀብታሙ ከጨዋታ ውጪ ሲሆን በተደጋጋሚ የታየው። ሲቀጥል ከሸንፈት ነበር የተመለስነው፤ ወላይታ ላይ ሜዳው አስቸጋሪ ስለነበር ቡድናችንን ሙሉ በሙሉ ማየት አልቻልንም። ቡድናችንን ለማየት በይበልጥ አጥቅተን ስለምንጫወትም ነው። በተደጋጋሚ ግብ ጋርም ሲሄዱ ስለነበር ለዛ ነው፡፡ ከእረፍት በኃላ ግን ይሄ አልነበረም፡፡ ወደ መከላከሉ ስንገባ የገባብንም ጎል አንድ ነው፡፡ እሱም የገባው ከእረፍት በፊት ነው ለጠየከኝ ጥያቄ የትኩረት ችግር ሳይሆን የመሀል ተከላካያችን በቶሎ ያለማቋረጡ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በስራ የሚስተካከል ነው፡፡

“ጎሎቹ የተቆጠሩብን ስናጠቃ ጎላችን ከፍተን ስለነበር ነው” መብራቶም ፍሰሀ – የስሑል ሽረ ም/አሰልጣኝ

ስለ ጨዋታው

የዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለታችንም በጣም ጠንካራ ነበርን። ጥንቃቄ የተሞላበት ጥሩ ጨዋታ ነበር፡፡ በዚህ ጥንካሬያችንም አንድ አቻ ነበርን፡፡ ሁለተኛ አጋማሽ እኛ በሰራናቸው የአቋቋም እና ቴክኒካል ስህተቶች ነው ጎሎቹ የተቆጠሩብን። ስናጠቃ ጎላችን ከፍተን ነበር፤ በዛም በመልሶ ማጥቃት እያገኙን በራሳችን የቦታ ስህተት አራት ለአንድ በሆነ ውጤት ተሸንፈናል፡፡

ከድል መልስ ሽንፈት

“በእግር ኳስ ያጋጥማል። አሁንም እኛ ነጥብ ጥለናል። ይሄን አስተካክለን እንመጣለን ምክንያቱም ክፈተታችንን አይተናል፡፡ የራሳችንም ስህተት ነው ብለን ተቀብለናል፡፡ ስንጫወት በሁለቱም በኩል ጥሩ ነው፡፡ ያሉብንን ክፍተቶች ላይ ደግሞ በደንብ ሰርተን እንዴት ለቀጣይ ሦስት ነጥብ እናግኝ የሚለው ላይ በደንብ እንሰራለን፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ