ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ በጎል ተንበሽብሾ ድሬዳዋ ከተማን አሸነፈ

በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የተከናወነው የባህር ዳር ከተማ እና የድሬደዋ ከተማ ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባህር ዳሮች በ3ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ወደ ሃዋሳ አምርተው ከተረቱበት ጨዋታ አንድ ተጨዋች ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሳለአምላክ ተገኝ በሚኪያስ ግርማ ተተክቶ ጨዋታውን አከናውኗል። በተገባዦቹ በኩል አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ በሜዳቸው የዓመቱን የመጀመሪያ ድል ካገኙበት የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ለጨዋታው ቀርበዋል።

አምስት ግቦች በተስተናገዱበት ጨዋታ ግብ መቆጠር የተጀመረው ገና በ4ኛው ደቂቃ ነው። በዚህ ደቂቃ የባህር ዳር ከተማ አዲስ ተጨዋቾች የሆኑት ማማዱ ሲዲቤ እና ፍፁም ዓለሙ ተቀባብለው ግብ ተቆጥሯል። የአማካይ መስመር ተጨዋቹ ፍፁም ከሲዲቤ የተለቀቀለትን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ በግራ እግሩ በማስቆጠር ነው ቡድኑን መሪ ያደረገው።

ገና በጨዋታው ጅማሮ ግብ ያስተናገዱት ተጋባዦቹ በ12ኛው ደቂቃ በሰነዘሩት ጥቃት አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በዚህ ደቂቃ ያሬድ ታደሰ ያገኘውን አጋጣሚ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ሀሪስተን ሄሱ አምክኖበታል። ጨዋታውን በሚፈልጉት መልኩ የጀመሩት ባህር ዳሮች በ17ኛው ደቂቃ በፈጠሩት የግርማ ዲሳሳ አጋጣሚ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ለማስፋት ሞክረው መክኖባቸዋል።

የስምዖን ዓባይ ድሬዳዋ ከተማ በ22ኛው ደቂቃ በተፈጠረ የቆመ ኳስ አቻ ሆኗል። በዚህ ደቂቃ የተገኘውን የቅጣት ምት ኤሊያስ ማሞ አሻግሮት ሪችሞንድ ኦዶንጎ አስቆጥሯል። የአቻነት ግብ ያስተናገዱት የጣናው ሞገዶቹ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አፀፋዊ ምላሽ ሰተው ዳግም መሪ ሆነዋል። ከመዓዘን የተሻገረውን ኳስ ግዙፉ የቡድኑ ተከላላይ አዳማ ሲሶኮ ወደ ግብ ከሞክረው የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ማማዱ ሲዲቤ በጭንቅላቱ ግብ አስቆጥሯል።

እስከ 24ኛው ደቂቃ ሶስት ግቦችን ያስተናገደው ጨዋታው በቀሪዎቹ የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች አስደንጋጭ የግብ ማግባት ሙከራዎች ሳይታዩበት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመስመር ላይ አጨዋወታቸውን ለማደስ ጥረት ያደረጉት ባለሜዳዎቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ እድሎችን ፈጥረው ታይቷል። በዚህም በ62ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ፍፁም ዓለሙ በድሬዳዋ ተከላካዮች ተደርባ የደረሰችውን ኳስ በመሞከር ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥሯል።

በዚህ አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በእጃቸው ያደረጉት የጣና ሞገዶቹ በ73ኛው ደቂቃ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሶስተኛ ግብ ባስቆጠረው ማማዱ ሲዲቤ አማካኝነት ባገኙት ኳስ መሪነታቸውን አስፍተዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ተጨዋቾች አራተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በ75ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፍፁም ከርቀት የመታትን ኳስ የድሬዳዋው ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን ለመቆጣጠር ተቸግሮ ኳስ እና መረብ ተገናኝቷል።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ባህር ዳሮች ጨዋታውን በራሳቸው መንገድ አከናውነው አሸናፊ ሆነዋል። በተቃራኒው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተጨዋች ቅያሪ ጨርሰው የነበረው ድሬደዋዎች በጎዶሎ ተጨዋች ጨዋታቸውን አገባደዋል።

ድሉን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማ ነጥቡን ሰባት አድርሶ ወደ ሦስተኛ ከፍ ሲል ከፍተኛውን ጎል እዳ ያስመዘገበው ድሬዳዋ ከተማ ወደ ወራጅ ቀጠናው ተመልሷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ