የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 1-2 መቐለ 70እንደርታ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት ጨዋታ በሆነው እና ሲዳማ ቡና በሜዳው መቐለ 70 እንደርታን ገጥሞ 2ለ1 ከተሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ተከታዩን አስታያየት ሰጥተዋል፡፡


“ዳኛው በእኛ ላይ ጫና እየፈጠረብንም ቢሆን አሸንፈናል” ገብረመድህን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ

ስለ ጨዋታው

ዛሬ ውጤቱ ያስፈልገን ነበር፤ ከሜዳችን ውጪ ብናገኝ ሶስት ነጥብ ካልሆነ አንድ ነጥብ ይዘን ለመውጣት ነበር እቅዳችን። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጥሩ ነው ውጤቱ። ታክቲክ የመረዳት፣ የመከላከል እና ተጫዋቾችን የመቆጣጠር አቅማችን ጥሩ ነበር። በልምምድ ላይ የሰራናቸውን ተግባራዊ ለማድረግም ሞክረዋል፡፡ ባለፉት ጨዋታዎች የመቀዛቀዝ ነገር ነበር፤ የታክቲክ ችግሮችም ነበሩ፡፡ ከቆሙ ኳሶችም ይገቡብን ነበር። አሁንም ግን የሚቆሙ ኳሶች እየበዙ ነው። ጥፋቶችም እየበዙ ነው፤ እኛ በሰራናቸው ሳይሆን ብዙ ጊዜ የዳኝነት ሁኔታም አለ። ከባድ ነበር ዛሬ፤ በዚህ ከባድ ሁኔታ አሸነፈን መውጣታችን መልካም ነው፡፡

ከግቡ በኋላ መቀዛቀዝ እና ወደ መከላከሉ ማዘንበል

ይሄን አጨዋወት የመረጠልን ዳኛው ነው። ዳኛው በእኛ ላይ ጫና እየፈጠረብንም ቢሆን አሸንፈናል፡፡ ስለዚህ ምንም ማድረግ አትችልም። ያንን ውጤት ጠብቀህ ለመውጣት የግድ መከላከል አለብህ። አንዳንዴ ደግሞ ሁኔታዎች ሳትፈልገው እንድትከላከል ያደርጉሀል። ከእዛ አንፃር እንጂ መርጠነው አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ፍርሀትም አለ ከነበርንበትም ለመውጣት ፡፡ በዳኝነቱ በጣም ጫና ፈጥሮብናል በሆነ ባልሆነ ቢጫ እየሰጠብን ስለነበር ያንን መቋቋም ከባድ ነው፡፡ በዳኝነቱ እንዲህ ሲደጋገምብህ መከላከሉ የግድ ነው፡፡ እየመራህም ስለሆነ አስጠብቀህ ለመውጣት መጣር የግድ ነው፡፡

“ከእረፍት በፊት መከላከል ላይ ልክ አልነበርንም” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ከእረፍት በፊት ወደ መከላከሉ ስንመጣ ልክ አልነበርንም፤ ክፍተት የተፈጠረው እዛ ጋር ነው። ስለዚህ ቀጣይ ላሉብን ጨዋታዎች የመከላከል ሂደታችንን አስተካክለን እንቀጥላለን። ከእረፍት በፊት በሰራናቸው የአቋቋም ስህቶች ግብ አስተናግደናል፡፡

ከእረፍት በኃላ ግን አርመን ገብተን የተሻልን ሆነናል። እነሱ አስጠብቆ ለመውጣት በራሳቸው ሜዳ ላይ ጊዜያቸውን አሳልፈዋል፡፡ እኛ የማስከፈት ስራ ስንሰራ እነሱ በዝተው ስለሚከላከሉ የምንፈልገው ነገር ማድረግ አልቻልንም። አንዳንድ ጊዜ በሜዳ ላይ የምትሰራው ስህተት ለተጋጣሚ በተለይ ለሚከላከል ቡድን አመቺ ይሆናል፡፡ እነሱ ከእኛ በእንቅስቃሴ ተሽለው ሳይሆን ከእረፍት በፊት በሰራነው ስህተት ያገኙት ጎል ነው እንድንሸነፍ ያደረገን፡፡ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ነው የተጠቀሙት፤ እኛ ባሰብነው መንገድ አላገቡብንም።

ግርማን ወደ መከላከል መልሰን ብርሀኑን የተጠቀምነው ማጥቃት ስለፈለግን ነው። ብርሀኑም ማጥቃት ላይ የተሻለ ስለነበር ከግርማ እሱን በሁለተኛው አጋማሽ ተጠቅመነዋል። መጀመሪያ ያልተጠቀምነው እነሱ ረጃጅም ኳሶችን ስለሚጫወቱ ግርማም እዛ ጋር ቢቆም የተሻለ ነው ብለን ስለላሰብን ነው


© ሶከር ኢትዮጵያ