ሪፖርት | መቐለ ከሜዳው ውጪ ጣፋጭ ሙሉ ነጥብ ጨበጠ

በአራተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩበት ግቦች በመቐለ 70 እንደርታ 2-1 ተሸንፏል፡፡

ባለሜዳው ሲዳማ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን ሲረታ ከተጠቀመው የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ዮሴፍ ዮሃንስን በአበባየው ዮሃንስ የለወጠ ሲሆን በተመሳሳይ መቐለ 70 እንደርታ በሜዳው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1-1 በተለያየበት ጨዋታ የተሰለፈው አስናቀ ሞገስን በአምበሉ አንተነህ ገብረክርስቶስ ተክቶ የዛሬውን ጨዋታ ጀምሯል፡፡

ፌዴራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሩት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድን ይዘው የገቡ ቢሆንም አዋጪ የማጥቃት ኃይላቸውን ግን በግልፅ መመልከት ያልቻልበት ነበር። ይሁንና ሲዳማ ቡና እንደ ወትሮው በዳዊት ተፈራ ይመራ የነበረው የአማካይ ክፍሉ ያለመረጋጋት ይታይበት የነበረ በመሆኑ በመልሶ ማጥቃት ወደ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ኦኪኪ አፎላቢ ላዘነበለው ምዓም አናብስት በቀላሉ ተጋላጭ ሆኗል፡፡ አጀማመራቸው በእንቅስቃሴ በተወሰነ መልኩ ያመረላቸው ሲዳማ ቡናዎች በቀኝ በኩል ሀብታሙ ገዛኸኝ በ7ኛው እና 10ኛው ደቂቃ በፈጣን ሽግግር የተገኙ ሁለት አጋጣሚዎችን ሞክሮ ግብ ጠባቂው ፊሊፕ ኦቮኖ አዳነበት እንጂ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር።

የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ የሲዳማን የአጨዋወት መንገድ በሚገባ የተረዱት መቐለዎች 20ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ በመሀል ሜዳ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ኳስ በሚቀባበሉበት ወቅት ኦኪኪ አፎላቢ በፍጥነት ከኃላ ደርሶ የነጠቃትን ኳስ በግራ አቅጣጫ አመቺ ቦታ ላይ የሲዳማ ቡና ተከላካዮችን የአቋቋም ስህተት በመጠቀም ለአማኑኤል ገብረሚካኤል አሳልፎለት አጥቂው በሚታወቅበት የማስቆጠር ብቃት ኳሷን እየነዳ ወደ ሳጥን በመግባት ግብ አድርጓታል፡፡

ግብ ካገቡ በኃላ አሁንም ሌላ ግብ ፍለጋ አፋጣኝ የመልሶ ማጥቃት አደረጃጀትን ለመጠቀም ያሰቡትን መቐለ 70 እንደርታዎች በድጋሚ የሲዳማ ቡናን ስህተት ተጠቅመዋል፡፡ 44ኛው ደቂቃ ያሬድ ከበደ መሀል ሜዳው ጨረር ላይ ከሀብታሙ ገዛኸኝ ላይ ኳስን ነጥቆ ጥቂት ከገፋት በኋላ ለአማኑኤል ሰጥቶት አማኑኤል የሲዳማን የተከላካይ መስመር መዘናጋት ተመልክቶ በድጋሚ ነፃ ቦታ ላይ ለቆመው ያሬድ አሳልፎለት ያሬድም ወደ ግብነት ለውጧት በሁለት ግቦች ልዩነት የመቐለን መሪነት አስተማማኝ አድርጓል፡፡

ሁለት ግብ በራሳቸው ግልፅ ስህተት ለማስተናገድ የተገደዱት ሲዳማ ቡናዎች የዕረፍት መውጫ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ በከፈቱት ማጥቃት በግራ የመቐለ የግብ ክልል ወደ ኃላ በተጠጋ ቦታ ላይ አንተነህ ገብረክርስቶስ በሀብታሙ ገዛኸኝ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ በረጅሙ ሲያሻማ አበባየው ዮሐንስ በግንባሩ ጨረፍ አድርጎ ግብ በማስቆጠር ሲዳማን ወደ ጨዋታው መመለስ የቻለች ግብ አግብቶ 2-1 በሆነ ውጤት መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በእረፍት ሰዓት የቡድኖቹ አባላት ወደ መልበሻ ክፍል በሚያመሩበት ወቅት የመቐለ 70 እንደርታ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ከእለቱ ዳኞች ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ የገቡ ሲሆን የቃላት ምልልሶችንም አስተውለናል።

ከዕረፍት ሲመለሱ እየተመሩ ከሜዳ የወጡት ሲዳማ ቡናዎች የተጫዋቾቻቸውን የጨዋታ ቦታ ከመለወጥ ባለፈ ቅያሪዎችንም አድርገው ገብተዋል፡፡ ተከላካዩ ሰንደይ ሙቱኩን አውጥተው በመሀል ሜዳ የነበረባቸውን ክፍተት ለመድፈን ብርሀኑ አሻሞን በማስገባት በተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ ሲጫወት የነበረው ግርማ በቀለን ወደ መሀል ተከላካይነት መልሰዋል፡፡ በአንፃሩ መቐለ 70 እንደርታዎች በመከላከሉ ቀዝቀዝ ብሎ የታየውን ቢያድግልኝ ኤልያስን አስወጥተው ጋናዊውን ተከላካይ ላውረንስ ኢድዋርድን ወደ ሜዳ ማስገባታቸው እና የመከላከል ቁጥራቸውን ከአማካይ ክፍሉ አሚኑ ነስሩን ወደ ኃላ በማስጠጋት ከፍ ማድረጋቸው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ማቀዳቸውን የሚያሳይ ነበር። የሲዳማ ቡና የበላይነት አመዝኖ በታየበት በዚሁ አጋማሽ የብርሀኑ አሻሞን መግባት ተከትሎ በረጅሙ ወደ አዲስ እና ሀብታሙ የሚጣሉ ኳሶች በተደጋጋሚ ይታዩ ነበር።

የመቐለ 70 እንደርታ አጥቂዎች እጅጉን ቀዝቅዘው በታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ ኦኪኪ አፎላቢ በግል ጥረቱ አግኝቶ መጠቀም ካልቻለባት አንድ አጋጣሚ ውጪ አብዛኞቹ ተጫዋቾች አፈግፍገው በመጫወት እና ሰዓት ለማባከን በተደጋጋሚ በመውደቅ አሳልፈዋል። በተቃራኒው ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩት ሲዳማዎች ደግሞ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ቸግሯቸዋል።

ከነዚህም ውስጥ በ59ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ በቀኝ በኩል በረጅሙ የጣለለትን ይገዙ ቦጋለ በግንባር መትቶ ኦቮኖ የያዘበት የሚጠቀስ ሲሆን ግብ ጠባቂው በዳዊት ተፈራ ተቀይሮ ከገባ በኃላ ኳስን ለመያዝ ጥረት ሲያደርግ የነበረው ሚካኤል ሀሲሳ ክፍተቶችን እየጠበቀ ከርቀት ያደረጋቸው ሦስት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችንም አምክኗል። በተጨማሪም 69ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል ከቅጣት ምት አዲስ ግደይ መትቶት ፊሊፕ ኦቮኖ እንደምንም ያወጣበት ኳስ ሲዳማ ቡናን አቻ ለማድረግ የተቃረበ ነበር፡፡

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና ፍፁም ብልጫን ወስዶ ቢጫወትም ጥቅጥቅ ብሎ መከላከልን አማራጩ ያደረገው የገብረመድህን ኃይሌ ቡድን 2ለ1 በማሸነፍ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ሙሉ ነጥብን ይዞ ወጥቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ