ድሬደዋ በጉዳት መታመሱን ቀጥሏል

ትናንት በ5ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግደው ያለ ጎል በአቻ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ ድሬዎች ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት አጥተዋል።

የውድድር ዓመቱን ብዙ ጎሎችን በማስተናገድ አንድ ጨዋታ አሸንፎ፣ በአንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቆ ሦስት ጨዋታ ላይ ሽንፈት በማስተናገድ አጀማመሩ ያላማረለት ድሬዳዋ ከተማ በርከት ያሉ ተጫዋቾች በጉዳት አለመኖራቸው በቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረሰ እንደሆነ ይነገራል። ምንም እንኳ አንጋፋው ግብጠባቂ ሳምሶን አሰፋ ከረጅም ጊዜ ጉዳቱ በኋላ አገግሞ ወደ ሜዳ መመለሱ መልካም ዜና ቢሆንም በአንፃሩ የክለቡ የቡድኑ ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾች ጉዳት ማስተናገዳቸው አሳዛኝ ዜና ሆኗል።

ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በግሉ ስኬታማ ዓመታትን እያሳለፈ የሚገኘው የኃላ ደጀኑ በረከት ሳሙኤል ጎድኑ ላይ የመሰንጠቅ ጉዳት አጋጥሞት ከእነ ህመሙ ወገቡን በፋሻ ታስሮ ወደ ሜዳ ቢገባም እስከ 72ኛው ደቂቃ ድረስ ተጫውቶ ከዚህ በላይ መቀጠል ባለመቻሉ በዘሪሁን አንሼቦ ተቀይሮ መውጣት ችሏል።

ሌላኛው የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች እየሆነ መምጣቱን በዚህ ዓመት በተጫወተባቸው ጨዋታዎች ላይ አቅሙን እያሳየ የሚገኘው ወጣቱ አጥቂ ሳሙኤል ዘሪሁን በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ 86ኛው ደቂቃ ላይ ባጋጠመው የእግር ጉዳት በዳኛቸው በቀለ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

ከዚህ ቀደም በጉዳት ሆነው ከሜዳ ከራቁት ተጫዋቾች በተጨማሪ የሁለቱ ቁልፍ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት አገልግሎት የማይሰጡ መሆናቸው ለድሬዳዋዎች የውድድር ዓመቱን ፈታኝ እንዳያደርግባቸው ተሰግቷል። የጉዳት መጠናቸው ለምን ያህል ጊዜ ከሜዳ እንደሚያርቃቸው ለጊዜው የታወቀ ነገር ባይኖርም ለሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቁ ተገምቷል።

በድሬዳዋ ከተማ በአሁኑ ወቅት ያሬድ ሀሰን፣ ምንያህል ተሾመ እና ረመዳን ናስር በጉዳት የማይጫወቱ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ