ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር በመጀመርያ ሜዳ ጨዋታው የዓመቱን የመጀመርያ ድል አሳክቷል

ኢትዮጵያ ፕሪምየር ለግ ዛሬ ከተካሄዱት ጨዋታዎች መካከል ጅማ ላይ የተደረገው የጅማ አባ ጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። 

ጅማ አባ ጅፋር በዚህ የውድድር ዓመት የስታዲየም ለውጥ በማድረግ የቀረበ ሲሆን ከሁለት የሜዳ ቅጣቶች በኋላ አንጋፋው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ባስገነባው አዲስ ስታዲየም የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል።

አባ ጅፋሮች ባለፈው ሳምንት ከወልዋሎ ነጥብ ከተጋራበት ስብስብ መካከል በፊት መስመር ላይ በብሩክ ገብረዓብ ምትክ ብዙዓየሁ እንደሻው በአሰላለፉ ሲካተት በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ከሽረ ጋር ያለ ጎል ከተለያየው ስብስብ ደስታ ደሙ በአብዱልከሪም መሐመድ፣ አቡበከር ሳኒ በሀይደር ሸረፋ እንዲሁም ጋዲሳ መብራቴን በዛቦ ቴጉይ ሜትክ ጨዋታውን ጀምረዋል።

በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ኳሱን ለቅዱስ ጊዮርጊስ በመተው በመልሶ ማጥቃት የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ እንግዶቹ በአንፃሩ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢኖራቸውም በዚህ ሒደት የጎል እድል ለመፍጠር ሲቸገሩ እና ወደ ማጥቃት ወረዳ ሲደርሱ ሲቆራረጥ ተስተውሏል። ጅማዎች ጎል ማስቆጠር የቻሉት ገና ጨዋታው ብዙ ሳይጓዝ ነበር። በ13ኛው ደቂቃ ምንተስኖት ወደ ኋላ የመለሰውን ኳስ አጥቂው ብዙዓየሁ እንደሻው በመቆጣጠር ወደ ጎልነት ቀይሮ ጅማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከጎሉ በኋላ በቀሪዎቹ የመጀመርያ አጋማሽ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን ለመጀመርያ ጊዜ በአሰላለፍ ውሰጥ ተካቶ ተጫወተው ደስታ ደሙ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ሞክሮ አግዳሚውን ታኮ ከወጣበት ሙከራ ውጪ በሁለቱም በኩል ሊጠቀስ የሚችል አስደንጋጭ የሚባል ሙከራ ሳይታይ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጤቱን ለመቀልበስ ያለመ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ አሜ መሐመድ እና አቤል እንዳለን በማስገባት ይበልጥ ለማጥቃት ጥረት አድርጓል። በ60ኛው ደቂቃም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በግራ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው ሄኖክ ከመስመር ወደ መሐል አጥብቦ በመግባት ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት የቀድሞ ክለቡ ላይ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት እንዲቀጥል አስችሏል።

ከጎሉ በኋላ በሁለቱም በኩል ጥሩ ሙከራዎች የታዩ ሲሆን በተለይ በጅማ በኩል ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ብዙዓየሁ እንደሻው በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠቃቂው ባህሩ ያዳነበት እንዲሁም በጊዮርጊስ በኩል በተመሳሳይ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ምንተስኖት አዳነ ሞክሮ የጎሉን ብረት ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አምረላ ደልታታ ከ14 ደቂቃዎች የሜዳ ቆይታ በኋላ ለጅማ አባ ጅፋር ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ያስገኘች ድንቅ ጎል ማስቆጠር ችሏል። አምረላ 80ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተላከለትን ኳስ ከግማሽ ጨረቃው አካባቢ በድንቅ ሁኔታ በቮሊ በመምታት ነበር የማሸነፍያዋን ጎል ያስቆጠረው።

ውጤቱን ተከትሎ የዓመቱ የመጀመርያ ሦስት ነጥቡን ያሳካው ጅማ አባ ጅፋር ደረጃውን ወደ አስረኛ ከፍ ሲያደርግ በተቃራኒው የመጀመርያ ሽንፈት እና ጎል ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ 11ኛ ዝቅ ብሏል።

*ማስተካከያ 

ሪፖርቱ ላይ ናትናኤል ተብለው የተጠቀሱ ቦታዎች ምንተስኖት አዳነ በሚል እንዲስተካከሉ ከይቅርታ ጋር እንጠይቃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ