የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 2-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በ5ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ አባ ጅፋር በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስን ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ጳውሎስ ጌታቸው እና ሰርዳን ዝቪጅሆቭ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

“ዘንድሮ ማንም ከእኔ ውጤት እንዳይጠብቅ”- ጳውሎስ ጌታቸው (ጅማ አባጅፋር)

ስለጨዋታው

“ቡድኑ ገና አዲስ ነው፤ የተመለከታችኃቸው ልጆች ወጣቶች እና ገና ሮጠው ያልጠገቡ ናቸው። ይሁንና በሀገሪቱ ትልቅ ክለብ የሆነውን ጊዮርጊስን ማሸነፍ ችለናል። ዋናው ቁም ነገር ከአካባቢው የተገኙትን 13 ተጫዋቾች ከሌሎች ወጣቶች ጋር ደባልቄ እየተገነባ የሚገኘው ቡድን በቀጣይ እየተዋሃዱ ሲሄዱ ጥሩ ነገር መስራት እንችላለን። የዛሬው ድልም ለቀጣይ ስራዎች መነሳሻ ይሆነናል።”

ያለ ውጭ ሀገር ዜጋ ተጫዋቾች እያስመዘገበ ስለሚገኘው ውጤት

“አምና ለኦኪኪ ኦፎላቢ ይከፈል የነበረው ደሞዝ ዘንድሮ ላይ የ15 ተጫዋቾች ደሞዝ ይከፍልልናል። የእኔ ዋነኛ አላማዬ ከጅማ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶችን በሂደት ለኢትዮጵያ ወጣትና ዋናው ብሔራዊ ቡድን ማስመረጥ ነው። ለዚህ ደግሞ ህዝቡ በትዕግሥት ሊጠብቀኝ ይገባል። ዘንድሮ ማንም ከእኔ ውጤት እንዳይጠብቅ። በእጄ የሚገኙትን የጅማ ልጆች ከፕሪምየር ተጫዋቾች አንፃር ምን እንደሚመስሉ መገምገም በቀጣይ ዓመት ዳብረው ሲመጡ ስለውጤት በዛን ወቅት መነጋገር እንችላለን። እኔ በሒደት እገሌ ወሳኝ ተጫዋቾች ምናምን የሚባል ነገር የሚል ነገር እንዲኖር አልፈልግም። ዋነኛ የጅማ ደጋፊ የሚፈልገው የራሱ ልጆች ሜዳ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ማየት ነው። የውጭ ሀገራት ተጫዋቾች ለደጋፊው ታሪክ ሆኖ አልፏል፤ ዘንድሮ ደግሞ በጅማ ልጆች ትዝታ ለመፍጠር እንሰራለን።”

ስለ ጅማ ደጋፊዎቹ

“ከዚህ ቀደም ብዙ ደጋፊ ባላቸው እንደ ባህር ዳር እና ኢትዮጵያ ቡና በመሰሉ ክለቦች ሰርቻለሁ። የጅማ ደጋፊ ስለምንም የማይጨነቅ በምንም ጉዳይ የማያስጨንቅህና በኳስ መዝናናት የሚፈልግ ደጋፊ ነው። ይህን የኳስ ጥማቱን ዘንድሮ ከፈጣሪ ጋር አረካለሁ ብዬ አስባለሁ።

“ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኃላ ነውና ወደ ጅማ የተመለስነው በቀጣይ ጅማ ጅማ የሚሸት ቡድን ገንብተን ደጋፊን ለማስደሰት እንሰራለን።”

“ተጫዋቾቻችን በሰሯቸው ስህተቶች ጨዋታውን እንዲያሸንፉ ሁለቱን ጎሎች በስጦታ ነው የሰጠናቸው” ሰርዳን ዜቪጅሆቭ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ስለጨዋታው

“በቅድሚያ ጅማዎች ጨዋታውን ስላሸነፉ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ ። ተጫዋቾቻችን በሰሯቸው ስህተቶች ጨዋታውን እንዲያሸንፉ ሁለቱን ጎሎች በስጦታ ነው የሰጠናቸው። በቀጣይ ስህተቶቻችን በማረም ወደፊት ለመጓዝ መጣር ይኖርብናል። ሊጉ ገና ረጅም ጉዞ ነው ወደፊት ብዙ ጨዋታዎች ይጠብቁናል። ይህን ጨዋታ ረስተን በቀጣይ በሜዳችን በምናደርገው ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ስለማግኘት ማሰብ ይኖርብናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ