ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መቐለ 70 እንደርታ እና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል 

ረፋድ ላይ በተደረገው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ መቐለ እና አዳማ አንድ ለአንድ አቻ ተለያይተዋል።

ማራኪ ጨዋታ እና ተቀራራቢ ፉክክር በታየበት ጨዋታ አዳማ ከተማዎች ከመስመር ለአጥቂዎች በሚሻገሩ ኳሶች ለማጥቃት ሲሞክሩ መቐለዎችም ለብቸኛ አጥቂዋ ዮርዳኖስ ምዑዝ በረጅሙ በሚሻገሩ ኳሶች ለማጥቃት ጥረት አድርገዋል። በዘጠነኛ ደቂቃም በመቐለ ሳጥን ጥፋት በመሰራቱ የተገኘው ፍፁም ቅጣት ምት ምርቃት ፈለቀ አስቆጥራ ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች።

ጥቂት ሙከራዎች በታዩበት ጨዋታ አዳማዎች በምርቃት ፈለቀ ሌላ የቅጣት ምት ሙከራ አድርገው ነበር። በአጋማሹ ወደ ግባቸው ተጠግተው በጥሩ ሁኔታ ከመከላከል አልፈው እንደ ቡድን ማጥቃት ያልቻሉት መቐለዎች በሂወት ኪሮስ እና ሳምራዊት ሃይሉ አማካኝነት አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር።

አጓጊ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በአመዛኙ የመቐለዎች ብልጫ የታየበት ነበር። ሴናፍ ዋቁማ ከመስመር አሻምታው በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ስታረግ የዋለችው ፍረወይኒ አበራ ባወጣችው ሙከራቸው የጀመሩት አዳማዎች ብዙም ሳይቆዩ በገነት ሀይሌ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የገቡት መቐለዎችም ብልጫ በወሰዱበት አጋማሽ በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም አስካለ ገብረፃድቅ ከቅጣት ምት ሞክራ መስከረም መንግስቱ የመለሰችው ሙከራ እና ሳምራዊት ሀይሉ ከረጅም ርቀት የሞከረችው ኳስ ይጠቀሳሉ። ከዚ በተጨማሪም ዮርዳኖስ ምዑዝ በሁለት አጋጣሚ ያመከነቻቸው ወርቃማ ዕድሎች በባለሜዳዎቹ በኩል አስቆጪ ነበሩ።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አልቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ መቐለዎች በዮርዳኖስ በርሀ አማካኝነት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥረው ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ