ዘንድሮም በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መካከል ብቻ የሚደረገው የ2008 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሊግ ዋንጫ (የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ ውድድር) የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይደረጋሉ፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ሁለት ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን በ9፡00 አርባምንጭ ከተማ ከአምናው የፍፃሜ ተፋላሚ ሀዋሳ ከተማ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ 11፡30 ላይ ደግሞ አምና በሩብ ፍፃሜው የተሰናበተው ኢትዮጵያ ቡና በታሪኩ የውድድሩን የመጀመርያ ጨዋታ ከሚያደርገው ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያደርጋል፡፡ ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታድየም 10፡00 ላይ ሊደረግ የነበረው የኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ አዳማ ከተማ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አድርጎ ከድሬዳዋ በቶሎ ባለመመለሱ ለነገ ተራዝሟል፡፡ በዚህም መሰረት ጨዋታው ነገ በ08፡00 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
የውድድሩ ጨዋታዎች ነገ አበበ ቢቀላ ስታድየም ሲቀጥሉ በ8፡00 ሲዳማ ቡና ከዳሽን ቢራ ሲጫወቱ በ10፡00 ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በ2007 ፕሪሚየር ሊግ 1ኛ እና 2ኛ የወጡት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደደቢት ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን የአምናው ቻምፒዮን መከላከያ ከ ወላይታ ድቻ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ መከላከያ ባለበት የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተራዝሟል፡፡
ፎቶ የአምናው ቻምፒዮን መከላከያ