የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድንን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ

ዛሬ ከሰዓት የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድንን አስመልክቶ የቡድኑ አሰልጣኝ እና አምበል መግለጫ ሰጥተዋል።

በሕንድ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ ለመካፈል ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው ብሄራዊ ቡድኑ በአሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ እና በቡድኑ አምበል ፋሲካ መስፍን አማካኝነት ስለ ዝግጅቱ ገለፃ አድርጓል።

በቅድሚያ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ ስለ ተጨዋቾች ምርጫ እና ስለዝግጅት ጊዜ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ” የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኜ ከተሾምኩበት ጊዜ ጀምሮ በስራ ላይ ነበርኩ። ከማክሰኞ ታህሳስ 21 ጀምሮም ተጨዋቾችን ወደ ሆቴል እንዲገቡ አድርገን ዝግጅቶችን አድርገናል። በቅድሚያ 41 ያክል ተጨዋቾችን ከየክለቦቹ መርጠናል። እነዚህን 41 ተጨዋቾች መርጠን ወደ መጀመሪያ ዙር ልምምድ ስንገባ ደግሞ በእድሜ እና በተለያዩ ምክንያቶች የተወሰኑ ተጨዋቾችን ቀንሰናል። ከዛም በሁለተኛው የልምምድ መርሃ ግብር በድጋሜ ተጨዋቾችን በብቃት እና በእንቅስቃሴ ቀንሰን ስብስባችንን 29 አድርሰናል። በመጨረሻ ልምምድ ደግሞ 6 ተጨዋቾችን ቀንሰን ስብስባችንን 23 አድርገናል።” ብለዋል።

አሰልጣኙ በመግለጫቸው ጨምረውም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጥሩ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አውስተዋል።


ከአሰልጣኙ ገለፃ በኋላ ቡድኑን በአምበልነት እንድትመራ እድለ የተሰጣት ፋሲካ መስፍን ሃሳቧን አካፍላለች። “የነበረን ጊዜ አጭር ቢሆንም አሰልጣኞቻችን የሚሰጡንን ስልጠና ተጠቅመን ጥሩ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን። በዝግጅታችን ጊዜ ሁለት አይነት ስልጠናዎች ናቸው የተሰጡን። አንደኛው የተግባር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የክፍል ውስጥ ስልጠና ነው። በተለይ በክፍል ውስጥ የሳይኮሎጂ ትምህርቶችንን ወስደናል። የቡድን ቅንጅቱም በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው። ከፈጣሪ ጋር ክፍተቶቻችንን እያሻሻልን የተሻለ ነገር ለማምጣት እንሞክራለን። በአጠቃላይ ግን እኛ ታዳጊ እንደመሆናችን ለወደፊት የሚጠቅሙንን ትምህርቶች እየወሰድን ሃላፊነት መውሰድን እንለማመዳለን።”ብላለች።
የቡድኑ አሰልጣኝ እና አምበል ይህንን አጭር መግለጫ ከሰጡ በኋላ በስፍራው ከተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎች ተቀብለዋል።

ተጨዋቾች ስለተመረጡበት እና ስለተቀነሱበት ሂደት?

41 ተጨዋቾችን የመረጥነው እኛ በምናቀው እና ከሌሎች አሰልጣኞች ጋር በመነጋገር ነው። ተጨዋቾችን ደግሞ የቀነስነው በአካላዊ እይታ እና በልደት ካርድ ነው። እንደ ህግ አንድ ብሄራዊ ቡድን የሜም አር አይ ምርመራ ማድረግ አለበት የሚል ግዴታ በሴት ታዳጊዎች ውድድር ላይ የለም። ዋናው መስፈርቱ የፓስፖርት እድሜ ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ግን በአህጉራዊ ውድድሮች የተለመዱ የእድሜ ማጭበርበሮች እንዳይኖሩ ትክክለኛ የእድሜ ማጣራቶች እንዲኖሩ አድርጓል። በከዚህ በተጨማሪ ተጨዋቾችን የቀነስነው በልምምድ ወቅት ባደረጉት እንቅስቃሴ ነው።

ስለ ቡድኑ እቅድ?

እንደማንኛውም ብሄራዊ ቡድን እቅድ አለን። የመጀመሪያ እቅዳችን የፊታችንን ጠንካራ የዩጋንዳ ጨዋታ ማሸነፍ ነው።

በዝግጅት ጊዜ ስለነበሩ ችግሮች?

አሁን ሁሉም ነገሮች ጥሩ ናቸው። ነገር ግን በቀጣይ መስተካከል ያለበት ነገር አለ። ይህም የዝግጅት ጊዜ ነው። ረዘም ያለ የዝግጅት ጊዜ ቢኖር እና አሰልጣኞች ተጨዋቾችን በደንብ ፈትነው ቢመርጡ መልካም ነው።

በመግለጫው ላይ ብሄራዊ ቡድኑ ነገ የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ለማከናወን ወደ ዩጋንዳ ካምፓላ እንደሚያመራ ተጠቁሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ