ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

ነገ ከሚደረጉ ቀሪ የ8ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነውን የአዳማ ከተማ እና የሃዋሳ ከተማ ጨዋታ የዳሰሳችን ማሳረጊያ አድርገነዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ መቐለ አምርተው የመጀመሪያ የሊጉ ሽንፈታቸውን ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች ኅዳር 27 በሜዳቸው ወልቂጤ ከተማን ያሸነፉበትን ብቸኛ ድል በአምሯቸው እያሰላሰሉ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የአዳማ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
ተሸነፈ አቻ አቻ አቻ አቻ

ከሌሎች ቡድኖች ይልቅ በስብስብ ደረጃ ያልተቀየረ ስብስብ ቢይዝም ያልተዋሃደ ቡድን እያስመለከተ የሚገኘው አዳማ ከተማ እጅግ ግቦችን የማስቆጠር ችግር ይታይበታል። እርግጥ ቡድኑ ከተለያዩ አማራጮች ተጋጣሚን ለማስጨነቅ ቢሞክርም ኳስ እና መረብን የማገናኘት አይናፋርነት ይስተዋልበታል። በተለይ በዳዋ እና በረከት ቅልጥፍና ታግዞ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ መስመር የሚደርሰው ቡድኑ የፍሬያማነት ችግር አለበት።

ቡድኑ ሦስት ነጥብ ካገኘ 36 ቀናት ስለተቆጠሩ በነገው ጨዋታ በይበልጥ ለማጥቃት እና ለማሸነፍ ታትሮ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል። በተለይ ከመስመር የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶችን እና የቆሙ ኳሶችን ወደ ግብነት ለመቀየር እንደሚጥር ይገመታል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በነገው ጨዋታ ሚካኤል ጆርጅን እና ብሩክ ቃልቦሬን በጉዳት እንደማያገኙ ሲጠቆም መጠነኛ ጉዳት ያስተናገደው አዲስ ህንፃ መሰለፉ አጠራጣሪ ነው ተብሏል።

እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በተከታታይ ከወልዋሎ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የጣሉትን ነጥብ ለማግኘት እና ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመምጣት አዳማ ገብተዋል።

የሀዋሳ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም
አቻ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ የሚሰለጥነው ቡድኑ የኋላ መስመሩን በመጠኑ የጠገነ ይመስላል። በተለይ የቡድኑ ግብ ጠባቂ ቢሊንጋ ኢኖህ በ4ኛ ሳምንት (በኢትዮጵያ ቡና) 4 ግቦች ካስተናገደ በኋላ የተነቃቃ ይመስላል።

የሁለቱ አጥቂዎቹን ቅልጥፍና በመጠቀም ተጋጣሚን የሚያስደነግጠው ቡድኑ በነገውም ጨዋታ የአጥቂዎቹን ፍጥነት እጅግ ይሻል። በተለይ ብሩክ እና እስራኤል የቡድኑን የፊት መስመር የሚመሩ ከሆነ አዳማዎችን በሙሉ ልብ እንዳያጠቁ እና የተመጣጠነ የተጫዋች ቁጥር በራሳቸው ክልል እንዲተው ሊያደርግ ይችላል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ቡድኑ የመከላከል አደረጃጀቱን ያስተካከለ ቢመስልም አልፎ አልፎ የሚስተዋልበት የመዘናጋት ችግር ነገ ችግር ውስጥ እንዳይከተው ያሰጋል።

ረዘም ያለ ጉዳት የገጠመው ቸርነት አውሽ እንዲሁም ባለፈው በቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ወሳኙ አጥቂ መስፍን ታፈሰ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ከጉዳት ተመልሶ የነበረው እስራኤል እሸቱ መሰለፉ አጠራጣሪ መሆኑ ተነግሯል፡፡

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች አስካሁን 37 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ 18 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ 8 ጊዜ ድል አድርጓል፡፡ በ11 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሀዋሳ 44 ጎሎች ሲያስቆጠር አዳማ ከተማ 36 አስቆጥሯል፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ጃኮ ፔንዜ

ሱሌይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሱሌይማን መሐመድ

አዲስ ህንፃ – አማኑኤል ጎበና – ከነዓን ማርክነህ

በረከት ደስታ – ዳዋ ሆቴሳ – ቡልቻ ሹራ

ሃዋሳ ከተማ (4-4-2)

ቤሊንጋ ኢኖህ

ዳንኤል ደርቤ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ – ኩዋሜ ኦሊቨር

አክሊሉ ተፈራ – ተስፋዬ መላኩ – አለልኝ አዘነ – ሄኖክ ድልቢ

ብሩክ በየነ – ሄኖክ አየለ


© ሶከር ኢትዮጵያ