‹‹ቀላል ጨዋታ ይሆናል ብለን አናስብም›› አዳነ ግርማ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጪው እሁድ ከሲሸልሱ ሴይንት ሚሼል ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ የልምምድ ሜዳ የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያም ከክለቡ ቁልፍ ተጫዋች አዳነ ግርማ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ስለ ዝግጅታቸው

‹‹ ለእሁዱ ጨዋታ ጥሩ ዝግጅት ነው ያደረግነው፡፡ ኢንተርናሽናል ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን ጨዋታው ትልቅ ጨዋታ ነው፡፡ አምና በጊዜ የተሰናበትንበትን ውጤት ለማስተካከልና ይህንን ቡድን አሸንፈን ወደ ቀጣዩ ዙር ለመግባት ተዘጋጅተናል፡፡ በጥሩ ውጤት ለማለፍ ደግሞ የግድ በሜዳችን ጨዋታውን መጨረስ ይጠበቅብናል፡፡ ››

ስለ ጨዋታው

‹‹ የመጀመርያዎቹን 20 እና 25 ደቂዎች ግብ ላናስቆጥር እችላለን፡፡ የመጀመርያው አጋማሽን ግብ ሳናስቆጥር ልንዘልቅም እንችላለን፡፡ ስለዚህ ደጋፊው ትዕግስት ሊያደርግ ይገባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጨዋታው የደርሶ መልስ ሲሆን ጨዋታውን እዚህ ጨርሰን እንድንሄድ ይፈለጋል፡፡ ይህ ፍላጎት ደግሞ እኛ ላይ ጫና ሊፈጥር ስለሚችል ደጋፊዎቻችን ትዕግስተኛ እንዲሆኑ እንዲሁም የምንወክለው ቅዱስ ጊዮርጊስን ብቻ ሳይሆን ሃገራችንን በመሆኑ ሙሉ 90 ደቂቃውን ከጎናችን እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ ››

ስለ ተጋጣሚያቸው

‹‹ሜዳ ውስጥ ከገባን በኋላ ቀላል የምንለው ጨዋታ የለም፡፡ ካሸነፍን በኋላ ነው ‹ቀላል ነበር› የምንለው፡፡ ስለዚህም አንዱን ክለብ ከፍ አንዱን ክለብ ዝቅ አድርገን የምናይበት ምክንያት የለም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሃገሪቱ ታሪካዊ እና ትልቅ ክለብ እንደመሆኑ መጠን ወደ ሜዳ የምንገባው ለማሸነፍ ነው፡፡

‹‹ የጨዋታው ውጤት ይህ ይሆናል ብለን ቀድመን መገመት አንችልም፡፡ አሁን የሚገኙበትን ሁኔታ እና ምን አይነት ቡድን እንደሆኑ አናውቅም፡፡  አብዛኛዎቹ የሴይንት ሚሼል ተጫዋቾች የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች እንደሚሆኑ አስባለሁ፡፡ ብሄራዊ ቡድንናችን ደግሞ ከሲሸልስ ጋር አቻ ተለያይቷል፡፡ ይህ ምን ያህል ጠንካራ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ስለዚህ ቀላል ጨዋታ ይሆናል ብለን አናስብም፡፡ ››

እሁድ ከአዳነ ምን ይጠበቃል?

‹‹ አጥቂ ተጫዋች እንደመሆኔ መጠን ለብሄራዊ ቡድንም ሆነ ለክለብ ስጫወት ከእኔ ሁልጊዜ ጎል ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ግብ የማስቆጠር ኃላፊነት አለብኝ፡፡ ግዴታየም ነው፡፡ ››

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *