ቅዱስ ጊዮርጊስ የሲሸልሹን ሻምፒዮን ሴንት ሚሸል ዩናይትድን ዕሁድ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ይገጥማል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ዛሬ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ በሚገኘው የክለቡ የመለማመጃ ሜዳ ተገኝታ ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ማርቲነስ ኢግናተስ ‘ኖይ’ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች፡፡
ስለዝግጅት
“ተቋርጠ ጦየቆየው ፕሪምየር ሊግ ከተጀመረ በኋላ ጨዋታዎችን በማድረግ ላይ ነበርን፡፡ ሁለት የሊግ ጨዋታዎችን ማድረግ ችለናል፡፡ አሁን በትክክለኛው መንገድ ላይ እንገኛለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ”
ስለጨዋታው
“ጨዋታው ቀላል ይሆናል የሚል ግምት የለኝም፡፡ በአፍሪካ እግርኳስ ውስጥ ለ16 ዓመታት በስራ ላይ ቆይቻለሁ፡፡ በነዚህ አጋጣሚዎች ክለቦችን እና ብሄራዊ ቡድኖችን አሰልጥኛለሁ፡፡ ሁሌም የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ ለማሸነፍ እንቅፋት ይበዛባቸዋል፡፡”
ስለክለቡ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቀጣይ ጉዞ
” መጀመሪያ ትኩረት ማድረግ ያለብን ከሴንት ሚሸል ጋር በደርሶ መልስ የሚደረገው ጨዋታ ላይ ነው፡፡ እኛም ነገሮችን ቀስ በቀስ እና ዙር በዙር ነው ማስኬድ የምንፈልገው፡፡ ”
ጊዮርጊስ ሴንት ሚሸልን ማሸንፍ ይችላል?
“ለ80ኛው ዓመት ክብረ በዓል በጥር ወር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከሱዳን ሊግ ሻምፒዮን (ኤል ሜሪክ) እና ከኬንያ ሊግ ሻምፒዮን (ጎር ማሂያ) ጋር አድርገናል፡፡ በጨዋታዎቹ ላይ ጥሩ የሚባል ውጤት ነበርን ስለዚህም ከሲሸልስ ሻምፒዮኖች ጋርም በተመሳሳይ ጥሩ ውጤት ሊኖረን ይገባል፡፡ “