ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሰንጠረዡ አናት የተጠጋበትን ድል ኤሌክትሪክ ላይ አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም 2 ጨዋታዎች ሲስተናገዱ 9 ሰዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያገናኘው ጨዋታ በፈረሰኞቹ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኤሌክትሪኮች በቋሚ አሰላለፍ በ4ኛው ሳምንት በወልዋሎ የ3-1 ሽንፈት ካጋጠመው ቡድናቸው የ2 ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ግርማ በቀለ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ስብስብ ውስጥ መካተቱን ተከትሎ ሲሴይ ሃሰን የመሰለፉን ዕድል ሲያገኝ ጥላሁን ወልዴ በተክሉ ተስፋዬ ተተክቷል። በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስም ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡናን ካሸነፈው ቡድኑ ፍሬዘር ካሳን በአብዱልከሪም መሐመድን ተክቶ  ወደ ጨዋታው ገብቷል።

በጨዋታው የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የሆነ የጨዋታ እንቅስቃሴ የነበረ ሲሆን በኤሌክትሪክ በኩል ከመስመር ተሻምተው በሮበርት ኦዶንካራ በቀላሉ ከተያዙ ኳሶች ውጪ ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎች ግን በሁለቱም በኩል አልተፈጠሩም። በ12ኛው ደቂቃ አሜ መሐመድ በግራ በኩል ያገኘውን ኳስ ወደግብ በቀጥታ በመምታት የጨዋታውን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ቢያደርግም በኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ ተመልሶበታል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሃይሌ እሸቱ የሮበርት ኦዶንካራ አቋቋም ተመልክቶ ከርቀት የሞከረውን ኳስ ሮበርት ተመልሶ አውጥቶበታል።

በ23ኛው ደቂቃ ኢብራሂማ ፎፋና ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ አድርጓል። ፈረሰኞቹ ከግቡ መቆጠር በኋላ በተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በ26ኛው ደቂቃ ሙሉዓለም መስፍን ከርቀት መትቶ የወጣበት፣ እንዲሁም ጋዲሳ መብራቴ በግራ በኩል ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ መትቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ።

ከዚህ በኋላ ኤሌክትሪኮች አንፃራዊ የጨዋታ ብልጫ ሲወስዱ በ37ኛው ደቂቃ ዲዲዬ ለብሪ 2 የቅዱስ ጊዮርጊስ ተሰላካዮችን አልፎ ከርቀት የመታው ኳስ በሮበርት በቀላሉ ተይዞበታል። የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃዎች ሲቀሩት በግራ መስመር ሙሉአለም መስፍን የሰራውን ስህተት ተከትሎ ኳስ ያኘኘው ዲዲዬ ለብሪ ወደ ሳጥኑ በመግባት ሲያሻግር ካሉሻ አልሃሰን አግኝቶ ወደግብ በመቀየር ኤሌክትሪክን አቻ አድርጓል፤ ግቡም በውድድር ዓመቱ ያስቆጠረው 4ኛ ግቡ ሆኖ ተመዝግቦለታል።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የኤሌክትሪክ የጨዋታ እና የግብ አጋጣሚዎች ብልጫ የቀጠለ ሲሆን በ46ኛው ደቂቃ ሃይሌ እሸቱ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳላህዲን ባርጌቾ ያስጣለበት አጋጣሚ፣ እንዲሁም በ50ኛው ደቂቃ አወት ገ/ሚካኤል ያሻማውን ኳስ ሄኖክ ካሳሁን በቮሊ ሞክሮ የወጣበት አጋጣሚዎች ለግብ የቀረቡ።

ቀስ በቀስ ወደጨዋታው የተመለሱት ፈረሰኞቹ ከደቂቃዎች በኋላ መሪነቱን ዳግም የጨበጡበትን ግብ በአብዱልከሪም ኒኪማ አማካኝነት ማግኘት ችለዋል። አብዱልከሪም ከግቡ 30 ሜትር አካባቢ ያገኘውን ኳስ የኤሌክትሪክ ተከላካዮችን ካሸማቀቀ በኋላ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሯል።

በ64ኛው ደቂቃ በዳኛ ላይ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ የ6 ወር ቅጣት ተላልፎበት የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ አዳነ ግርማ ቅጣቱን አጠናቅቆ አሜ መሃመድን በመለወጥ ወደ ሜዳ ተመልሷል። አዳነ በ72ኛው ደቂቃም አብዱልከሪም መሃመድ በቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ ግብ  የሞከረውን እና የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ዮሃንስ በዛብህ የመለሰውን ኳስ ከመረብ ላይ በማሳረፍ ልዩነቱን ማስፋት ችሏል።

በቀሪ ደቂቃዎች ሁለቱም ክለቦች ጥሩ የሚባሉ የግብ ዕድሎችን ያመከኑ ሲሆን በ75ኛው ደቂቃ ጥላሁን ወልዴ ከሳጥኑ ውጪ ወደግብ ሞክሮ ሮበርት በጣቶቹ ያወጣበት ኳስ ኤሌክትሪክ ያደረገው የሚጠቀስ ሙከራ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስም በኩል አብዱልከሪም ኒኪማ ከርቀት መትቶ በግብ ጠባቂው የተመለሰበት፣ እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሃይሉ አሰፋ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ዮሐንስ በዛብህ ከመስመሩ በመውጣት ያከሸፈበት ኳሶች ጥሩ የግብ ዕድሎች ነበሩ።

ውጤቱን ተከትሎ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች የሚቀሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደረጃውን ወደ 3ኛ ሲያሻሽል በ4 ጨዋታዎች 4 ነጥቦችን ብቻ መሰብሰብ የቻለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 15ኛ ደረጃን ይዟል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ስደተኞች በሊቢያ የሚደርስባቸውን አሰቃቂ ተግባራት የሚቃወም ባነር ይዘው ገብተዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *