ወልዋሎ ከሦስት ተጫዋቾች ጋር ለመለያየት ተስማማ

በጥር ዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾች ያስፈረሙት ወልዋሎዎች ከፍቃዱ ደነቀ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ምስጋናው ወልደዮሐንስ ጋር ለመለያየት በቃል ደረጃ ተስማምተዋል። በቀጣይ ቀናትም ሒደቱ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው የክረምት ዝውውር መስኮት ቡድኑን ተቀላቅለው ላለፉት ስድስት ወራት ክለቡን ያገለገሉት እነዚህ ሦስት ተጫዋቾች በቀድሞ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድን ውስጥ ወሳኝ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች እንደነበሩ ይታወሳል።

በክረምቱ ከመጀመርያ ፈራሚዎች አንዱ የነበረው ምስጋናው በመጀመርያው ዙር በቀኝ ተከላካይ መስመር ተቀዳሚ ተመራጭ ሆኖ በሁሉም ጨዋታዎች ተሰልፎ ተጫውቷል። ሁለተኛው በስምምነት የተለያየው ተከላካዩ ፍቃዱ ደነቀ በጉዳት ከሜዳ እስከራቀበት ግዜ ድረስ የተከላካይ ክፍሉን በቋሚነት የመራ ሲሆን በተወሰኑ ጨዋታዎችም በአማካይነት ተሰልፎ ቡድኑ ማገልገሉ ይታወሳል። ሶስተኛ ከቡድኑ ጋር በስምምነት የሚለያየው ካርሎስ ዳምጠው ቡድኑ በሊጉ ጅማሬ ላይ ላሳየው ወጥነት ያለው ብቃት ጥሩ አበርክቶ የነበረው ሲሆን በግማሽ ዓመት የቡድኑ ቆይታው ሁለት ጎሎች በማስቆጠር እና ሁለት በማመቻቸት በአራት ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል።

© ሶከር ኢትዮጵያ