የከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎች

በእረፍት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግን የተመለከቱና ሰሞኑን የተሰሙ አጫጭር የዝውውር፣ የቅጣት፣ የቅሬታ እና የአሰልጣኞች መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናቸዋል።

የቅጣት ውሳኔዎች

ጌዴኦ ዲላ

በምድብ ሐ የካቲት 22 ዲላ ላይ የተደረገው የጌዴኦ ዲላ እና ቡታጅራ ከተማ ጨዋታ ላይ በተፈፀመው የስፖርታዊ ጥሰት የዲሲፕሊን ኮሚቴው ዲላን ሁለት የሜዳው ጨዋተዎችን በገለልተኛ ሜዳ እንዲያደርግ እና 40 ሺህ ብር እንዲከፍል ቅጣት አስተላልፎበታል።

ኮሚቴው በቅጣት ማብራርያው ላይ እንደገለፀው በጨዋታው 72ኛ ደቂቃ ረዳት ዳኛውን በውሀ በተሞላ ፕላስቲክ ተማትተው ጉዳት በማድረስ ጨዋታው ለ6 ደቂቃዎት እንዲቋረጥ በማድረጋቸው፤ በ89ኛው ደቂቃ ዲላዎች ጎል ሲያስቆጠር ሁለተኛ ረዳት ዳኛቸው ላይ ድንጋይ በመወርወራቸው በድጋሚ ለ15 ደቂቃዎች የተቋረጠ መሆኑ እንዲሁም የረብሻው ምክንያት የዲላ ክለብ ደጋፊዎች መሆናቸው በጨዋታ አመራሮች ሪፖርት በመደረጉ የቅጣት ውሳኔው ተላልፏል።

ቡታጅራ ከተማ

በምድብ ሐ የሚገኘው ቡታጅራ ተጫዋቾች የነበሩት ሙባረክ ያሲን እና ቢኒያም ግርማ ደሞዛቸው ህጋዊ ባልሆነ ምክንያት መቋረጡን በመግለፅ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት የዲሲፕሊን ኮሚቴው ከዚህ ቀደም ያሳለፈው ውሳኔ (የተጫዋቾቹ ደሞዝ ተከፍሎ ወደ ቡድኑ እንዲመለሱ) ባለመተግበሩ ውሳኔውን ተፈፃሚ እስኪያደርግ ድረስ ከፌዴሬሽኑ ማንኛውንም አገልግሎት እንዳያገኙ ታግዷል።

የዝውውር መረጃዎች

አርባምንጭ ከተማ

የምድብ ሐ መሪ የሆኑት አዞዎቹ በድሩ ኑርሁሴንን አስፈርመዋል። ቁመተ መለሎው የቀድሞ የወልዲያ አጥቂ ዘንድሮ በደሴ ከተማ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በቶጓዊው አጥቂ ኤደም ኮደዞ ላይ የተንጠለጠለውን የጎል ማስቆጠር ኃላፊነት እንደሚጋራ ይጠበቃል።

ሻሸመኔ ከተማ

በምድብ ለ እየተፎካከረ የሚገኘው ሻሸመኔ ከተማ አራት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። አማካይ ቦታ ላይ የሚጫወተው ምትኩ ጌታቸው ከጌዴኦ ዲላ፣ የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን፣ መከላከያ እና ደቡብ ፖሊስ የፊት መስመር ተጫዋች ማናዬ ፋንቱ ፣ የቀድሞ የኤሌክትሪክ የጅማ አባቡና እንዲሁም በ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫውቶ ያሳለፈው ዳንኤል ራህማቶ እንዲሁም ከደሴ ከተማ በአጥቂ ስፍራ ላይ የሚጫወተው መልካሙ ፉንዱሬን ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል።

ወሎ ኮምቦልቻ

በምድብ ሀ እየተፎካከረ የሚገኘው ወሎ ኮምቦልቻ ዐቢይ ቡልቲን አስፈርሟል። የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ዘንድሮ በገላን ከተማ ያሳለፈ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ እየተፎካከረ ለሚገኘው ኮምቦልቻ የፊት መስመር ጥንካሬ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

ደደቢት

በምድብ ሀ የሚገኘው ደደቢት ከሁለት ተጫዋቾች በስምምነት ተለያይ ብሩክ ገብረአብ እና ሲሳይ ጥበቡን ለማስፈረም ተስማምቷል። ሰማያዊዎቹ በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ሰዓት ካስፈረሙት ዘላለም ሊካሲ እና ላለፈው አንድ ዓመት ከስድስት ወር ከቡድኑ ጋር ቆይታ የነበረው ዓብዱልዓዚዝ ዳውድ ጋር ነው በስምምነት የተለያዩት።

በአሁኑ ሰዓት ከፌዴሬሽኑ አገልግሎት እንዳያገኝ እገዳ ላይ የሚገኘው ደደቢት ለወልዋሎ ፈርሞ በግል ጉዳይ የተለያየው ብሩክ ገብረአብ እንዲሁም በመጀመርያው ዙር ከወሎ ኮምቦልቻ ጋር ቆይታ የነበረው ግዙፉ ተከላካይ ሲሳይ ጥበቡን ለማስፈረም የተስማማ ሲሆን እግዱ ሲነሳ ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሶሎዳ ዓድዋ

ባለፈው ክረምት ሶሎዳ ዓድዋን ለቆ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ክለብ መቐለ 70 እንደርታ በማምራት ላለፉት ወራት ከፕሪምየር ሊጉ ክለብ ቆይታ ያደረገው ክብሮም አፅብሀ ከወራት ቆይታ በኃላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ሶሎዳ ዓድዋ ተመልሷል። ባለፈው የውድድር ዓመት በብሔራዊ ሊጉ በርካታ ግቦች አስቆጥሮ ሶሎዳዎች ወደ ከፍተኛ ሊጉ እንዲያድጉ ትልቅ አስተዋፅኦ የነበረው ይህ አጥቂ በስድስት ወር የውሰት ውል ነው ወደ ቀድሞ ክለቡ የተመለሰው።

በተያያዘ ዜና ዓድዋዎች በክረምቱ ካስፈረሟቸው መብራህቱ ኃይለሥላሴ እና ቃልአብ ኪዱ ጋር ተለያይተዋል። ተጫዋቾቹን ያሰናበተበት ምክንያት በስነ-ምግባር ጉድለት እንደሆነ በፌስቡክ ገፁ ያስታወቀው ቡድኑ በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾች እንደሚያስፈርም ገልፅዋል።

ቅሬታዎች

ጌዴኦ ዲላ

የምድብ ሐ ተሳታፊው ጌዲኦ ዲላ ተጫዋቾች የ3ወር ደሞዝ እንዲሁም ጥቅማ ጥቅም ሳይከፈለን እስካሁን ቆይተናል። ጉዳዩን እግርኳስ ፌዴሪሽኑ እንዲፈታልን በማለት 27 ተጫዎቾች የክፍያ ጥያቄን ለፌዴሬሽኑ ማስገባታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ደሴ ከተማ

አራት የቀድሞ የደሴ ተጫዋቾች ውል እያላቸው በክለቡ በኩል መቋረጡ አግባብ አይደለም በማለት በ19/05/2012 የፍትህ አካላት የወሰኑት ውሳኔ እንዲፈፅሙ የተፃፈ ደብዳቤ ለክለቡ ያልደረሰ መሆኑን በመግለፅ ቡድኑ ከዚህም በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ ቢሰጥም እንዳልሰጠ ሆኖ መገለፁ አግባብ እደዳልሆነ ቅሬታውን አሰምቷል። ፌዴሬሽኑ የመዝገብ ቤት አሰራሩን በትኩረት ሊፈትሽ ይገባዋል በማለት ጉዳዩን በይግባኝ እንደተያዘ ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።

የአሰልጣኞች መረጃ

ኢትዮጵያ መድን

የምድብ ሐ ተሳታፊው ኢትዮጵያ መድን ከአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ ጋር መለያየቱን ተከትሎ ግርማ ታደሰን አዲስ አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል። ከሀዲያ ሆሳዕና (2 ጊዜ) እና ደቡብ ፖሊስ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ በማደግ የሊጉ ውጤታማ አሰልጣኝ የሆኑት ግርማ ከወራት በፊት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን በምድብ ሐ እየተቸገረ የሚገኘው መድንን ውጤት የማሻሻል ከባድ ኃላፊነትን ተረክበዋል።

ደሴ ከተማ

የደሴ ከተማ አሰልጣኝ አረጋይ ወንድሙ ከክለቡ ጋር ለመለያየት መወሰናቸውን ባስገቡት የመልቀቂያ ይዘት ያለው ደብዳቤ ገልፀዋል። ከአቅም በላይ የሆነ ጉዳይ ገጥሟቸው ከክለቡ ለመለያየት እንደወሰኑ የገለፁ ሲሆን ክለቡ በአንፃሱ ያለ ፍቃድ ውል እያላቸው ከቡድኑ መራቃቸውን ተከትሎ ቅጣት ሊተላለፍባቸው እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ሀምበሪቾ

የምድብ ለ ክለብ የሆነው ሀምበሪቾ ዱራሜ ዋና አሰልጣኙ ዓለማየሁ አባይነህን አሰናብቷል። የቀድሞው የአርባምንጭ እና ሲዳማ ቡና አሰልጣኝ አምና ወደ ክለቡ በማምራት ውጤቱ እንዲሻሻል መርዳታቸውን ተከትሎ ዘንድሮ ጠንካራ ቡድን ይዘው ይቀርባሉ ተብለው ቢጠበቁም በጠንካራው ምድብ ተፎካካሪ ለመሆን ተቸግረው ታይተዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ