ሳላዲን ሰዒድ ህክምና ተደርጎለት ከሆስፒታል ወጥቷል

ሳላዲን ሰዒድ ከጥቂት ደጋፊዎች ጋር በተፈጠረ ግብግብ እጁ ላይ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታል አምርቶ የነበረ ሲሆን አሁን በተሻለ ጤንነት ይገኛል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሰበታ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኃላ ሳላዲን ሰዒድ ለሶከር ኢትዮጵያ በሜዳ ላይ በተፈጠረው ድርጊት ዙርያ አስተያየት መስጠቱን እና ይቅርታ መጠየቁን መዘገባችን ይታወቃል። ሆኖም ይህን ዘገባ ካጠናከርን በኋላ ሁለት ደጋፊዎች ሳላዲን ሰዒድ ወደ ሰርቪስ እያመራ ባለበት ሁኔታ ለድብደባ በመጋበዝ በተፈጠረ ግርግር ሳላዲን በእጁ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት እና ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል በማምራት ህክምና ተደርጎለት ማምሻውን በጥሩ ጤንነት ከሆስፒታሉ እንደወጣ ሰምተናል።

በሳላዲን ሰዒድ ላይ ይህን ድርጊት የፈፀሙት ሁለቱ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙ መሆናቸውን ለማወቅ የቻልን ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎች ካሉ እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ