ሪፖርት | ባህር ዳሮች በግብ ጠባቂው አስደናቂ ብቃት ታግዘው ከመቐለ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል

ሀሪስተን ሄሱ ድንቅ ብቃት ባሳየበት ጨዋታ ምዓም እናብስት እና የጣና ሞገዶቹ ነጥብ ተጋርተዋል።

መቐለዎች ባለፈው ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን ካሸነፈው ስብስብ ቢያድግልኝ ኤልያስን በአስናቀ ሞገስ ተክተው ሲገቡ ባህር ዳር ከተማዎችም ጅማን ከረታው ስብስብ ስንታየሁ መንግሥቱን በማማዱ ሲዲቤ ተክተው ገብተዋል።

የመቐለዎች ሙሉ ብልጫ የታየበት እና ቤኒናዊ ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ሄሱ የጣና ሞገዶቹን የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑ ባስመሰከረበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ በርካታ ሙከራዎች ያደረጉበት እንግዶቹ ደግሞ ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩበት ነበር።

ከረጅም ጊዜ በኃላ ወደ 4-2-3-1 አደራደር የተመለሱት መቐለዎች የብዙዎች ግምት ባፋለሰ መልኩ በባህር ዳር ከተማ ላይ ፍፁም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። ቡድኑ ካደረጋቸው በርካታ ሙከራዎችም አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከዮናስ ገረመው የተላከለትን ኳስ በነፃ አቋቋም ሆኖ መቶ ሀሪሰን ሄሱ በጥሩ ሁኔታ ያወጣው እና ኦኪኪ አፎላቢ ከመሀል ሜዳ አከባቢ ለአማኑኤል አሾልኮለት አጥቂው ከሀሪሰን ሄሱ አንድ ለአንድ ተገናኝቶ መቶ ግብ ጠባቂው በአስደናቂ ብቃት ግብ ከመሆን ያዳነው ሙከራ ይጠቀሳሉ።
በጨዋታው በቀላሉ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ደርሰው ጥቃቶች ለመሰንዘር ያልቦዘኑት ባለሜዳዎቹ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም በቁጥር በርካታ የሆኑ የግብ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም አማኑኤል በድጋሚ ከሀሪሰን ሄሱ ጋር ተገናኝቶ ወደ ውጭ ያወጣት ኳስ፤ ካሉሻ አልሀሰን ከመስመር የተሻማውን ኳስ በግንባር ገጭቶ ሀሪሰን እንደምንም የያዘው እና ኦኪኪ ኦፎላቢ በሁለት አጋጥሚዎች አክርሮ መቷቸው ኮከብ ሆኖ የዋለው ሀሪስተን ሄሱ እንደምንም ያዳናቸው ኳሶች በምዓም አናብስት በኩል የተፈጠሩ የግብ ሙከራዎች ነበሩ።

በመጀመርያው አጋማሽ የተጋጣሚያቸው የማጥቅያ መንገዶችን መከላከል አቅቷቸው በርካታ የግብ ሙከራዎች ያስተናገዱት የጣና ሞገዶቹ ምንም እንኳ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በተወሰኑ አጋጣሚዎች አስደንጋጭ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ዳንኤል ኃይሉ ከርቀት አክርሮ መቶ አግዳሚው የመለሰለት ኳስ እና ሳላምላክ ተገኘ በመጀመርያው ደቂቃ ሞክሮት ፍሊፕ ኦቮኖ ያመለሰው ኳስ ይጠቀሳሉ። ግርማ ዲሳሳ ከቅጣት ምት በቀጥታ መቷት በተከላካዮች የትኩረት ችግር ግብ ለመሆን ተቃርባ የነበረችውም ሙከራም ሌላ ተጠቃሽ ናት።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የባለሜዳዎቹ ብልጫ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ እንግዳው ቡድን ባህርዳር ከተማ ማሻሻያዎች ሳያደርግ ገብቶ በተመሳሳይ የተቸገረበት ነበር። ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የተለየ ለውጥ ሳያደርጉ በገቡበት አጋማሽ መቐለዎች ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ተጨማሪ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት የጣና ሞገዶቹም ከረጅም ርቀት በሚመቱ ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉበት ነበር።

ካሉሻ አልሀሰን ባደረገው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ባለሜዳዎቹ በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ወደ ሜዳ ገብተው ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመስመር አሻምቶት ኦኪኪ አፎላቢ በግንባር ገጭቶ የግቡን ብረት ለትሞ የተመለሰው ኳስ እና ያሬድ ከበደ ከኦኪኪ አፎላቢ የተላከለትን ኳስ መቶ ከግቡ አቅራብያ የነበረው አቤል ውዱ ጨርፎ ወደ ውጭ ያወጣው ኳስ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ያሬድ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ሞክረው ሀሪሰን ሄሱ ያዳናቸው ሙከራዎችም መቐለን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ለማጥቃት ፍላጎት የሌለው እና በቅጡ የማይከላከል ቡድን ይዘው የቀረቡት ባህርዳሮች ምንም እንኳን አመርቂ እንቅስቃሴ ባያሳዩም ያደረጓቸው ጥቂት ሙከራዎች ግን አስቆጪ ነበሩ። በተለይም ፍፁም ዓለሙ ከመሐል ሜዳ ይዟት የመጣውን ኳስ አክርሮ መቶ ፍሊፕ ኦቮኖ እንደምንም ያወጣት እና ግርማ ዲሳሳ እና ሰለሞን ወዴሳ ከርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በጨዋታው የሀሪሰን ሄሱ እና የዮናስ ገረመው ድንቅ ብቃት እንዲሁም የባህርዳር ከተማ ደጋፊዎች የማያቋርጥ ድጋፍ ትኩረት ሳቢ ነበሩ። ጨዋታው በዚህ መልኩ ያለ ጎል መጠናቀቁን ተከትሎም መቐለዎች የሊጉን መሪ የሚሆኑበት ዕድል ሲያባክኑ ባህርዳር ከተማዎች ወሳኝ አንድ ነጥብ አሳክተው ነጥባቸው ሀያ ሰባት አድርሰዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ