የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-1 ሀድያ ሆሳዕና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንዲህ ሰጥተውናል፡፡

“ተጫዋቾቹ ጋር የነበረው ችግር ምን እንደሆነ አላውቅም” የሀዋሳ ከተማ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ብርሀኑ ወርቁ

ስለጨዋታው

“ጨዋታውን እንደጠበቅነው አይደለም ያገኘነው። እነሱም እኛም ተሸንፈን ነው የመጣነው። እኛ ሜዳችን ላይ የማሸነፍ አቅም ነበረን። ሆኖም ዛሬ ትንሽ ተቀዛቅዘን ነበር የገባነው። በዛም ምክንያት ውጤት ልናጣ ችለናል፡፡ ልጆቹ ጋር የነበረው ችግር ምን እንደሆነ አላውቅም። ወደ ዛሬው ጨዋታ ከመግባታቸው በፊት የሚያሳዩት ነገር ጥሩ ነው። ሜዳ ላይ የነበረው ደግሞ የሚታይ ነው። ከዚህ ቀደም የነበራቸው ነገር አውጥተው እየተጫወቱ አይደለም። ይህ መነሻው ምን እንደሆነ ግን አላውቅም፡፡ ”

ተቀይሮ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ የገባው አቤኔዘር ዮሐንስ በተደጋጋሚ ኳስን ወደ ኃላ እየተመለሰ ስለፈጠራቸው ስህተተቶች

“የተባለው ትክክል ነው። አጨዋወቱ ወደ ኃላ ነበር። ይህ የተፈጠረበት ምክንያት ደግሞ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ተዳክመው ነበር፡፡ የተሻሉ ብለን የምናስባቸው ሲኒየሮች ደግሞ ጉዳት ላይ ስለነበሩ አብዛኛዎቹን ታዳጊ ነው የተጠቀምነው። ከስኳድም አንፃር ቡድኑ ጠባብ ስለሆነ ነው የተጠቀምነው። ለጨዋታው አዲስ ነው፤ የተነገረውን አልነበረም ሲተገብር የነበረው። የግሉን ነገር ነው ሲያንፀባርቅ የነበረው። ግን ወደፊት የሚስተካከል ነው፡፡

“ሽንፈት ላለማስተናገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገን ነበረ የመጣነው” ፀጋዬ ኪዳነማርያም (ሀዲያ ሆሳዕና)

ስለጨዋታው

“እንግዲህ ሁለታችንም ተሸንፈን ነበር የመጣነው። ሁለተኛ ሽንፈት ላለማስተናገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገን ነበር የመጣነው። ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው በኳስ ቁጥጥሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ነው ወደ ሜዳ ይዘን የገባነው፡፡ በአጠቃላይ እንደ ሀዲያ ሆሳዕና እየተወዳደርን ቡድን እየሰራን ነው ያለነው ማለት ይቻላል፡፡ ዛሬ እንግዲህ ወደ ቡድኑ የቀላቀልናቸው አራት ተጫዋቾችን ለመጠቀም ሞክረናል፡፡ በአንደኛው ዙር እና በሁለተኛው ዙር ያለብንን ክፍተቶቻችንን ለመድፈን ተጫዋች ለማምጣት ነው የሞከርነው። ልጆች ብናመጣም ያው ከዝግጅት አንፃር ሁለት እና ሶስት ቀን ነው ከቡድኑ ጋር የሰሩት እና የቅንጅት እና የውህደት ችግር አለባቸው። ያም ሆነ ይህ ቀሪ የሀያ ቀን ዕረፍት ስላለ ያን ሰዓት በማስተካከል ቋሚ ቡድናችንን እንፈጥራለን።

” በአካል ብቃት ረገድ ያልተስተካከሉ አሉ፤ በዝግጅት ወቅት ይሄን ለማሻሻል እንሞክራለን፡፡ አጨራረሳችን ግን የአጭር ጊዜ ሳይሆን የረጅም ጊዜ ችግራችን ነው፡፡ ፎፋና ጨራሽ አጥቂ ብለን ነው በሁለተኛው ዙር ከሽረ ያመጣነው። እሱ እንግዲህ ዛሬ ገና ሁለት ልምምድ ነው የሰራው ማለት ይቻላል፡፡ አንድ ሙሉ እና አንድ ቀላል ነው የሰራው። ከአማካዮች ጋር ውህደት እና ቅንጅት በቶሎ ይኖረዋል ብለን አናስብም። ዞሮ ዞሮ ወደ ግብ መድረሳችን አንድ ነገር ነው። ብዙ ጊዜ የግብ ዕድሎችን እየፈጠርን ነው ያለነው። በቀላሉም ደግሞ የሚገባበት ቡድንም አይደለም። ግን የተገኙትን ዕድች ያለ መጠቀም ችግር ነው። ይሆን ደግሞ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ”

© ሶከር ኢትዮጵያ