ወልቂጤ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሷል

በዝውውር መስኮቱ ከሀዋሳ እና መቐለ ጋር የተለያዩት ተስፋዬ መላኩ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ለወልቂጤ ለመፈረም ተቃርበዋል።

ሀዋሳ ከተማን በክረምቱ ተቀላቅሎ ከሁለት ቀናት በፊት በስምምነት ቀሪ የአምስት ወራት ውል እየቀረው የተለያየው ሁለገቡ ተስፋዬ ዘንድሮ ወደ ሀዋሳ ከተማ ከማምራቱ በፊት ወደ ወልቂጤ ከተማ ለማምራት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ሳይፈርም ቀርቶ ወደ ሀዋሳ ያመራ ሲሆን ክለቡን ከሰሞኑ ከለቀቀ በኋላ ለወልቂጤ ከተማ ለመጫወት ተስማምቷል። ነገ በይፋ እንደሚፈርም የሚጠበቀው የቀድሞው የወላይታ ድቻ፣ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና ጅማ አባጅፋር ተከላካይ በጉዳት እና የተለያዩ ምክንያቶች ክፉኛ የሳሳው የወልቂጤ ተከላካይ መስመር ላይ አማራጭ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

የመስመር አጥቂው ሳሙኤል ሳሊሶ ሌላው ወልቂጤ ከተማን ለመቀላቀል ከጫፍ የደረሰ ተጫዋች ነው። የቀድሞው የሼር ኢትዮጵያ ተጫዋች ዓምና መከላከያን በመልቀቅ ወደ መቐለ 70 እንደርታ በማምራት የ18 ወራት ቆይታ ያደረገ ሲሆን የስድስት ወራት ኮንትራት እየቀረው ባስገባው የመልቀቂያ ደብዳቤ መሠረት ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቶ ወደ ደግአረግ ይግዛው ቡድን ለማምራት በቃል ደረጃ ተስማምቷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ