አስራ ሁለት ተጫዋቾች ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል

የደደቢት ፣ ወልዋሎ ፣ መቐለ እና ሽረ ተጫዋቾች በጋራ ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚሆን ድጋፍ አደረጉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለበርካታ የሰው ሂወት ማለፍ ምክንያት የሆነው እና ለተለያዩ ውድድሮች መቋረጥ ምክንያት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ለመከላከል የቅዱስ ጊዮርጊስ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን እና በግል ደረጃ ካርሎስ ዳምጠው በግሉ ድጋፎች ማድረጋቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ በደደቢት፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ በመጫወት የሚገኙት ሄኖክ ገብረመድኅን፣ አንተነህ ገብረክርስቶስ፣ ሙሴ ዮሐንስ፣ ኃይለአብ ኃይለሥላሴ፣ ዮናስ ግርማይ፣ ሶፎንያስ ሰይፈ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ፣ ኃይሉ ገብረየሱስ፣ ቢንያም ደበሳይ፣ ክብሮም ግርማይ ፣ያሬድ ከበደ እና አሸናፊ ሀፍቱ ለወረርሺኙ መከላከያ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

በቀጣይ ቀናትም ሌሎች ተጫዋቾች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ተግባር የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በመንቀሳቀስ ላይ ለሚገኙ የወጣቶች ማኅበራት የሚበረከት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ