ታሪክ የሰራው ትውልድ ፊት አውራሪ – ትውስታ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አንደበት

ኢትዮጵያ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ በአፍሪካ መድረክ እንድትሳተፍ በፊት መሪነት ትልቁን ሚና የተወጡት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የዛሬው የትውስታ አምዳችን እንግዳ ናቸው።

ቆፍጣና እና ልበ ሙሉ አሰልጣኝ ናቸው። ለረጅም ዓመታት በአሰልጣኝነት ዘመናቸው በስኬት እና በተግዳሮት የተሞላ ጊዜ አሳልፈዋል። በአደይ አበባ የጀመረው የአሰልጣኝነት ህይወታቸው በህዝብ ማመላለሻ ኮርፖሬሽን ፣ ጭነት ማመላለሻ ድርጅት(ጭማድ) ፣ መብራት ኃይል ፣ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ጉምሩክ፣ ሙገር፣ ኒያላ፣ እርሻ ሰብል እንዲሁም የመን ድረስ ዘልቋል። ከየመን መልስ ደግሞ በ2003 በክለብ አሰልጣኝነት ህይወታቸው የመጨረሻ የሆነው ትራንስ ኢትዮጵያን አሰልጥነዋል።

በቀልድ የተዋዛ ቁምነገር መለያቸው የሆነው አሰልጣኝ ሰውነት በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በ1978 የወጣት ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ፣ በ1989 የታዳጊ ወጣት ብሔራዊ ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ፣ በ1993 ዓ.ም የታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ፣ በ1994 የዋናው ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ፣ በ1997 በድጋሚ የብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ፣ በ1998 ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እና የዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል። ቀጥሎም በ2002 መጨረሻ የቶም ሴንትፌይት ምክትል ሆነው ወደ ብሔራዊ ቡድን የተመለሱ ሲሆን ከሦስት ወራት በኋላ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ተሹመው እስከ ጥር 14 ቀን 2006 ድረስ ቆይተዋል። በቆይታቸውም 3 የሴካፋ ዋንጫ ፣ 1 የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እና የቻን ተሳትፎን አሳክተዋል። በተለይ በሁሉም ስፖርት ወዳድ ቤተሰብ ሁሌም የሚታወሰውን ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያለፈችበት ክስተት የታሪካቸው ትልቁ ስኬት ነው። የዚህ ቡድን ፊት አውራሪ የነበሩት የአሰልጣኙ በዛሬው የትውስታ አምዳችን ወደ ኃላ መለስ ብለው ሁኔታውን እንዲህ ያስታውሱታል።

” ይህን ታሪክ ለማሳካት ሠላሳ አንድ ዓመት ሙሉ የለፋሁበት ፣ የተሰደብኩበት፣ ‘ምን ይችላል ? ‘ ተብዬ ብዙ ተቃውሞ ያስተናገድኩበት ፣ ‘ኳስ የት ተጫውቶ ያውቃል ? ‘ በሚል እና ‘የት የተማረውን ነው ?’ እያሉ ብዙ ስሜን ያጠፉበት ነው። ይህን ሁሉ ፈተና እያለፍኩ ፈጣሪዬ አንድ ክብር ሳላገኝ ማሰልጠኔን አላቆምም ብዬ ሠላሳ አንድ ዓመት በትዕግስት የጠበኩበት ታሪኬ ነው። የነበሩትም ተጫዋቾች እንደ ቡድን በአንድ ልብ ታሪክ ለመስራት የነበረን ከፍተኛ ፍላጎት ይህን ለማሳካት በቅተናል። ከዛ በኃላ ለምን ማሰልጠን ተውኩኝ ? ዳሽን ቢራ ከፍተኛ ብር አቅርቦልኝ ነበር። በዚህ ዓመት መጀመርያ እንኳ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይ አካል ደውለው ‘የፈለከውን እንስጥህ አሰልጥን’ ብለውኝ ነበር። እኔ ግን አልፈልግም ፤ ማሰልጠን አቁሜያለው ከዚህ በኃላ ታዳጊዎችን በማሰልጠን ቀሪውን ጊዜዬን አሳልፋለው የምፈልገውን ክብሬን አግኝቻለው። የልፋቴን ውጤት አግኝቻለው። የእኔ ልብ ስለረካ ፣ ቤተሰቤ ስለተደሰተ ፣ እኔ የሚወደኝ ሰው ሁሉ አንገቱን ቀና አድርጎ መሄድ ከጀመረ ከዚህ በኃላ ለገንዘብ ብዬ ተመልሼ እራሴን ሌላ ነገር ውስጥ አልከትም ብዬ ነው ማሰልጠን ያቆምኩት። ጥቅምት አራት ለእኔ የዘመናት ህልሜን ያሳካሁበት ፣ የዘመናት ቁስሌ የተሻረበት የደስታ ቀኔ ነው። ይህ ታሪክ ዳግመኛ ጠንክሮ ከተሰራ የሚደገምበት ቀን ሩቅ አይሆንም። ግን በሁሉም አካላት ዘንድ ትልቅ ስራ ይጠብቃል።”

ጋሽ ሰውነት በአሁኑ ወቅት ክለብ ማሰልጠን በማቆም በግላቸው የታዳጊዎች አካዳሚ በመክፈት እያሰለጠኑ ከመሆናቸው በተጨማሪ የካፍ ኢኒስትራክትር በመሆን የተለያዩ የአሰልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ይሰጣሉ። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ እና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ